Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ጴጥሮስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፥ መጻተኞች ሆናችሁ በጳንጦስ፥ በገላትያ፥ በቀጰዶቅያ፥ በእስያ፥ በቢታንያ ተበታትናችሁ ለምትኖሩት

2 እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ በዐቀደው መሠረት ለተመረጣችሁት፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመታዘዝና በደሙ ተረጭታችሁ ለመንጻት በመንፈስ ቅዱስ ለተቀደሳችሁት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።


ሕያው ተስፋ

3 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን፥ በታላቅ ምሕረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤

4 እርሱም የማይጠፋውን፥ የማይበላሸውንና የማያረጀውን ርስት በሰማይ አዘጋጅቶላችኋል።

5 እናንተም በመጨረሻው ቀን ለሚገለጠው መዳን በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል።

6 ምንም እንኳ የተለያዩ ፈተናዎች ለጥቂት ጊዜ የሚያስቸግሩአችሁ ቢሆኑ በእርሱ ደስ ይበላችሁ።

7 ይህ ፈተና የሚደርስባችሁ የእምነታችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው፤ የሚጠፋ ወርቅ እንኳ በእሳት ይፈተናል፤ ከወርቅ ይልቅ የከበረ እምነታችሁ እንደዚሁ መፈተን አለበት፤ ይህም የተፈተነ እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፥ ክብርንና ውዳሴን ያስገኝላችኋል።

8 ኢየሱስ ክርስቶስን ያላያችሁት እንኳ ብትሆኑ ትወዱታላችሁ፤ አሁን እንኳ የማታዩት ብትሆኑ ታምኑበታላችሁ፤ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል።

9 በእምነታችሁም የምትጠብቁትን የነፍሳችሁን መዳን ታገኛላችሁ።

10 ስለዚህ መዳን ጉዳይ የእናንተ ስለሚሆነው ጸጋ የተነበዩት ነቢያት ጥልቅ ምርምርና ጥናት አድርገዋል።

11 ከእነርሱ ውስጥ የነበረውም የክርስቶስ መንፈስ በመሲሑ ላይ ስለሚደርሰው መከራና ከመከራውም በኋላ ስለሚያገኘው ክብር አስቀድሞ አመልክቶ ነበር፤ እነርሱም ይህ ሁሉ በምን ጊዜና በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሚሆን መርምረው ነበር፤

12 እነዚህ ነቢያት ያገለግሉ የነበሩት እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳልነበረ ተገልጦላቸዋል፤ ያገለገሉአችሁም ከሰማይ በተላከው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት አሁን ወንጌልን ያበሠሩአችሁ ሰዎች የነገሩአችሁን በመግለጥ ነው፤ ይህን ነገር መላእክት እንኳ ለማየት ይመኙት ነበር።


በቅድስና ስለመኖር

13 ስለዚህ ልቡናችሁን አንቅታችሁ ለሥራ ተዘጋጁ፤ በመጠን ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ለምታገኙት ጸጋ ሙሉ ተስፋ ይኑራችሁ።

14 ታዛዦች ልጆች ሆናችሁ ባለማወቅ ቀድሞ የነበራችሁን ክፉ ምኞት አትከተሉ፤

15 ነገር ግን የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤

16 “እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል።

17 ለማንም ሳያዳላ ለያንዳንዱ እንደየሥራው የሚፈርደውን እግዚአብሔርን “አባታችን” ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ በዚህ ዓለም በእንግድነት መጻተኞች ሆናችሁ ስትኖሩ እርሱን በመፍራት ኑሩ።

18 እናንተ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ አኗኗር የተዋጃችሁት ጠፊ በሆነ በብር ወይም በወርቅ አለመሆኑን ታውቃላችሁ።

19 እናንተ የተዋጃችሁት ነውር ወይም እንከን እንደሌለው ንጹሕ በግ በሆነው በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።

20 እርሱ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፥ አሁን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገልጦአል።

21 እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በኢየሱስ አማካይነት እርሱን ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ትተማመናላችሁ።

22 ለምእመናን ቅንነት የተሞላበት ፍቅር እንዲኖራችሁ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችኋል፤ ስለዚህ በሙሉ ልባችሁ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።

23 ዳግመኛ የተወለዳችሁት ሕያው በሆነውና ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤

24 መጽሐፍ እንደሚለው፦ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ዱር አበባ ነው፤ ሣሩም ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤

25 የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይኸው ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos