1 ቆሮንቶስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ጋብቻ የተሰጠ መመሪያ 1 ስለ ጻፋችሁልኝ ጥያቄ ሰው ከሴት ጋር ግንኙነት ባያደርግ መልካም ነው። 2 ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት የራስዋ ባል ይኑራት። 3 ባል ለሚስቱ ማድረግ የሚገባውን የጋብቻ መብትዋን አይከልክላት፤ እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ማድረግ የሚገባትን የጋብቻ መብቱን አትከልክለው። 4 ሚስት በሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ በእርስዋ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያለው ባልዋ ነው። እንዲሁም ባል በሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ በእርሱ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ነች። 5 በጸሎት ለመትጋት ሁለታችሁም ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር በመለያየት አንዱ የሌላውን የጋብቻ መብት አይከልክል። በዚህም ምክንያት ራሳችሁን መቈጣጠር አቅቶአችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደገና አብራችሁ ሁኑ። 6 ይህን ግን የምላችሁ እንደምክር ነው እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። 7 ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሚስት ሳያገባ ቢኖር በወደድኩ ነበር፤ ነገር ግን ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር የተለየ ስጦታ ሰጥቶታል፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ፥ ሌላውም ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። 8 ላላገቡና እንዲሁም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች የምለው እንዲህ ነው፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ መልካም ነው። 9 ነገር ግን በሥጋ ምኞት ከመቃጠል ይልቅ ማግባት የተሻለ ነውና ራሳቸውን መቈጣጠር ቢያቅታቸው ያግቡ። 10 ላገቡት ግን የምሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ያገባች ሴት ከባልዋ አትለይ፤ 11 ብትለይም ሳታገባ ለብቻዋ ትኑር፤ ወይም ከባልዋ ጋር ትታረቅ፤ እንዲሁም ባል ሚስቱን አይፍታ። 12 ለሌሎቹ ግን ጌታ ሳይሆን እኔ ራሴ የምለው እንዲህ ነው፤ አንድ ክርስቲያን ሰው ክርስቲያን ያልሆነች ሚስት ብትኖረውና አብራው ለመኖር ብትፈልግ አይፍታት። 13 ክርስቲያን ሴት ክርስቲያን ያልሆነ ባል ቢኖራትና አብሮአት ለመኖር ቢፈልግ አትፍታው። 14 ክርስቲያን ያልሆነ ባል ክርስቲያን በሆነች ሚስቱ ምክንያት የእግዚአብሔር ወገን ይሆናል፤ ክርስቲያን ያልሆነች ሚስትም ክርስቲያን በሆነው ባልዋ ምክንያት የእግዚአብሔር ወገን ትሆናለች፤ እንደዚህ ካልሆነማ ልጆቻችሁ የእግዚአብሔር ሰዎች ሊሆኑ አይችሉም፤ በዚህ ዐይነት ከኖራችሁ ግን ልጆቻችሁ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። 15 ክርስቲያን ያልሆነ ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ በዚህ ጊዜ ግን ክርስቲያን የሆነው ወገን ባልም ሆነ ሚስት በምንም ዐይነት ግዴታ አይያዝም። እግዚአብሔር የጠራን በሰላም እንድንኖር ነው። 16 አንቺ ክርስቲያን ሴት፥ ክርስቲያን ያልሆነውን ባልሽን ምናልባት ታድኚው እንደ ሆነ ምን ታውቂያለሽ? አንተስ ክርስቲያን ወንድ፥ ክርስቲያን ያልሆነች ሚስትህን ምንአልባት ታድናት እንደ ሆንክ ምን ታውቃለህ? እግዚአብሔር ሲጠራ በነበሩበት ሁኔታ መጽናት እንደሚገባ 17 እያንዳንዱ ጌታ በሰጠው ስጦታና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህንኑ ነው። 18 ማንም ሰው ከተገረዘ በኋላ የተጠራ ከሆነ እንዳልተገረዘ ለመሆን አያስብ፤ ሳይገረዝ የተጠራ ከሆነም መገረዝን አይፈልግ። 19 መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ዋጋ የለውም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው። 20 ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። 21 እግዚአብሔር በጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርክን? ብትሆንም ግድ የለም፤ አትጨነቅበት፤ ነጻ የመውጣት ዕድል ብታገኝ ግን ይህ ዕድል አያምልጥህ። 22 ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ ሰው በጌታ ነጻነትን አግኝቶአል፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። 23 እግዚአብሔር በዋጋ ስለ ገዛችሁ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። 24 ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ በነበረበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ጋር በዚያ ይኑር። ስላላገቡና ባሎቻቸው ስለ ሞቱባቸው ሴቶች የቀረበ ጥያቄ 25 ስላላገቡ ሰዎች ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት እምነት የሚጣልብኝ እንደ መሆኔ መጠን የራሴ ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፤ 26 አሁን ያለንበት ጊዜ የችግር ጊዜ ስለ ሆነ ሳያገቡ በብቸኝነት መኖር መልካም ይመስለኛል፤ 27 ሆኖም ሚስት አግብተህ እንደ ሆነ ለመፍታት አትፈልግ፤ ሚስት አላገባህ እንደ ሆነ ለማግባት አትፈልግ። 28 ነገር ግን አንተ ሚስት ብታገባ ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም፤ እንዲሁም አንዲት ልጃገረድ ባል ብታገባ ኃጢአት ይሆንባታል ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ የኑሮ ችግር ይገጥማቸዋል፤ የእኔም ምኞት ከዚህ ችግር እንድትድኑ ነው። 29 ወንድሞች ሆይ! እኔ የምላችሁ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ አጥሮአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያለችው ሚስት እንደሌለችው ሆኖ ይኑሩ። ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌሉአቸው ሆነው ይኑር። 30 የሚያዝኑም እንደማያዝኑ፥ የሚደሰቱ እንደማይደሰቱ ሆነው ይኑሩ፤ ዕቃ የሚገዙ፥ ምንም ዕቃ እንደሌላቸው አድርገው ይቊጠሩ። 31 በዚህ ዓለም ሀብት የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ሆነው ይኑሩ፤ የአሁኑ ዓለም ሁኔታ አላፊ ነው። 32 ስለዚህ በምንም ሐሳብ ሳትጨነቁ እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው ጌታ የሚደሰትበትን ነገር ስለሚፈልግ አሳቡ የሚያተኲረው፥ ጌታን በሚመለከት ሥራ ላይ ነው። 33 ሚስት ያገባ ሰው ግን የሚያስበው ስለዚህ ዓለም ነገርና ሚስቱንም የሚያስደስትበትን ነገር ነው። 34 በዚህ ሁኔታ ሐሳቡ በሁለት ተከፍሎአል ማለት ነው። እንዲሁም ባል ያላገባች ሴት ወይም ልጃገረድ በሥጋዋና በነፍስዋ ተቀድሳ የጌታ ለመሆን ስለምትፈልግ ሐሳቧ የሚያተኲረው ጌታን በሚመለከት ሥራ ነው። ያገባች ሴት ግን ባልዋን ለማስደሰት ስለምትፈልግ የምታስበው የዓለምን ነገር ነው። 35 እኔ ይህን የምላችሁ በወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ እንድትቸገሩ ብዬ ሳይሆን እንድትጠቀሙ ብዬ ነው፤ ምኞቴም እናንተ በተገቢው ሁኔታ እንድትኖሩና አሳባችሁ ሳይባክን በሙሉ ልባችሁ ጌታን እንድታገለግሉ ነው። 36 አንድ ሰው እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ በኋላ ይህን ማድረጉ ለልጅትዋ መልካም ያላደረገ መሆኑ ቢሰማው፥ ከዚህም ሌላ እርስዋን ለማግባት ያለው ፍላጎት ጠንካራ ቢሆንና መጋባታቸውም ትክክል ከመሰለው እንደ ተመኘው ቢያገባት ኃጢአት አይሆንበትም፤ ስለዚህም ይጋቡ። 37 ነገር ግን አንድ ሰው በልቡ ከጸና፥ አስገዳጅ ነገር ከሌለበት፥ ፍላጎቱን ለመቈጣጠር ከቻለና እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ መልካም አደረገ። 38 ስለዚህ ሚስት የሚያገባ መልካም ያደርጋል፤ የማያገባ ግን የተሻለ ያደርጋል። 39 ሚስት ባልዋ በሕይወት እስካለ ድረስ በጋብቻ ሕግ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ከሞተ ግን የፈለገችውን ለማግባት ነጻ ነች፤ ሆኖም የምታገባው ሰው ክርስቲያን መሆን አለበት። 40 በእኔ አስተያየት ግን ባል ሳታገባ ብቻዋን ብትሆን ይበልጥ ተደስታ ትኖራለች፤ እኔም የእግዚአብሔር መንፈስ ያለኝ ይመስለኛል። |