ምሳሌ 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በረዶ በበጋ ወራት፥ ዝናብም በመከር ወራት እንደማያስፈልግ ሁሉ ለሞኝ ክብር አይገባውም። 2 ወፎች ወዲያና ወዲህ ሲበርሩ ምንም ጒዳት ሊያደርሱብህ እንደማይችሉ ሁሉ ከንቱ ርግማንም ምንም ጒዳት አያመጣብህም። 3 ፈረስን መግረፍ በቅሎንም መለጐም እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሰነፍንም መቅጣት ያስፈልጋል። 4 የማይረባ ጥያቄ ለሚያቀርብልህ ሞኝ ሰው፥ አንተም እንደ እርሱ ሞኝ እንዳትሆን መልስ አትስጠው። 5 ሆኖም ጠቢብ ነኝ ብሎ እንዳይመጣ ሞኝነቱን በመግለጥ መልስለት። 6 ሞኝን መልእክተኛ ማድረግ የገዛ እግርን እንደ መቊረጥና ዐመፅን እንደ መጋበዝ ይቈጠራል። 7 ሞኝ በምሳሌ የሚጠቀመው ሽባ ሰው በአንካሳ እግሮቹ የሚጠቀመውን ያኽል ነው። 8 ለሞኝ ክብርን መስጠት ድንጋይን በወንጭፍ ላይ አጥብቆ አስሮ ለመወንጨፍ እንደ መሞከር ነው። 9 የሞኝ በምሳሌ መናገር ሰካራም በእጁ ላይ የተሰካውን እሾኽ ለማውጣት እንደ መታገል ያለ ነው። 10 በመንገድ የሚተላለፉትን ሞኞች ወይስ ሰካራሞች ሁሉ የሚቀጥር አሠሪ ያገኘውን ሰው ሁሉ እንደሚያቈስል ቀስት ወርዋሪ ነው። 11 ሞኝነቱን ደጋግሞ የሚገልጥ ሞኝ ሰው ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ነው። 12 በራሱ አስተሳሰብ ጠቢብ የሆነ ከሚመስለው ሰው ይልቅ ሞኝ ሰው ተስፋ አለው። 13 ሰነፍ ሰው “አንበሳ በመንገድ ላይ አለ፤ የሚያስፈሩ አንበሶች በጐዳናዎች ይዘዋወራሉ” ይላል። 14 መዝጊያ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር ሰነፍም በአልጋው ላይ መገላበጥ ያበዛል። 15 አንዳንድ ሰዎች በጣም ሰነፎች ናቸው፤ ሌላው ቀርቶ በወጥ ያጠቀሱትን እንጀራ መጒረስ ያታክታቸዋል። 16 ሰነፍ፥ በቂ ማስረጃ ከሚሰጡ ከሰባት ሰዎች ይበልጥ አስተዋይ የሆነ ይመስለዋል። 17 በማይመለከትህ ነገር መከራከር በመንገድ የሚተላለፈውን የውሻ ጆሮ እንደ መያዝ ይቈጠራል። 18-19 ሰውን አታሎ “በቀልድ ነው ያደረግኹት” የሚል ሰው በአደገኛ የጦር መሣሪያ እንደሚጫወት ዕብድ ሰው ነው። 20 እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሿኪ ከሌለም ጠብ ይቆማል። 21 ከሰል ፍምን፥ እንጨትም እሳትን እንደሚያበዛ ጠብ አጫሪ ሰው ጠብን ያባብሳል። 22 የአሾክሻኪ ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሰኘ እስከ ውስጥ ሰውነት ይወርዳል። 23 በልቡ ክፋት እያለ በአንደበቱ ልዝብ ቃል የሚናገር ሰው ውጪው በሚያምር በብር ቀለም እንደ ተቀባ የሸክላ ዕቃ ነው። 24 ተንኰለኛ ሰው በአፉ ይሸነግላል፤ በልቡ ግን ተንኰልን ያውጠነጥናል። 25 እርሱም ልቡ በጥላቻ የተሞላ ስለ ሆነ፤ በሚያባብል ቃል ቢያቈላምጥህም አትመነው፤ 26 ጥላቻውን ቢሰውርም፥ የሚያደርገው ክፉ ነገር በሰው ሁሉ ዘንድ ግልጥ ነው። 27 ለሌሎች ወጥመድን የሚዘረጉ ሰዎች ራሳቸው ይያዙበታል፤ በሰው ላይ የሚሰዱት የድንጋይ ናዳ እነርሱን መልሶ ይጐዳቸዋል። 28 ዋሾ አንደበት የሚጐዳቸውን ሰዎች ይጠላል፤ የሽንገላ ንግግርም ጥፋትን ያመጣል። |