1 ቆሮንቶስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሠተ መለያየት 1 ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ሳስተምራችሁ ሥጋውያንና በክርስቶስ ገና ያልጠነከራችሁ ሕፃናት እንደ መሆናችሁ መጠን ነው እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ መጠን አይደለም። 2 ጠንካራ ምግብ መብላት እንደማይችሉ ሕፃናት ስለ ሆናችሁ እኔ የመገብኳችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ምግብ መመገብ ገና የማትችሉ ናችሁ። 3 እናንተ አሁንም ገና ሥጋውያን ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ስለምትቀናኑና ስለምትከራከሩ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? የምትሠሩትስ እንደ ተራ ሰው አይደለምን? 4 አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ሲል ተራ የዓለም ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? 5 ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? እነርሱ እናንተ እንድታምኑ ያደረጉአችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ እያንዳንዳቸው የሚያገለግሉትም ጌታ ለያንዳንዳቸው በመደበላቸው ሥራ ነው፤ 6 እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። 7 ስለዚህ ለሥራው ዋና የሆነው ተክሉን ያሳደገው እግዚአብሔር ነው እንጂ የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ ምንም አይደለም። 8 የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ እኩል ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላል። 9 እኛ ለእግዚአብሔር አብረን የምንሠራ አገልጋዮች ነን፤ እናንተም የእግዚአብሔር እርሻና የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ። 10 እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም እኔ በጣልኩት መሠረት ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት። 11 አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ማንም ሌላ መሠረት መጣል አይችልም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 12 በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፥ ወይም በብር በከበረ ድንጋይ፥ ወይም በእንጨት፥ በሣር ወይም በገለባ የሚገነባ ቢኖር 13 የእያንዳንዱ ሰው ሥራ የሚገለጥበት የፍርድ ቀን ይመጣል፤ በዚያን ቀን የእያንዳንዱ ሰው ሥራ ምን ዐይነት እንደ ሆነ በእሳት ተፈትኖ ይገለጣል። 14 አንድ ግንበኛ በመሠረቱ ላይ የሠራው ሥራ በእሳት ተፈትኖ ሳይጐዳ ጸንቶ ከቆመ ግንበኛው ዋጋውን ያገኛል። 15 ሥራው በእሳት ተቃጥሎ የተደመሰሰበት ግንበኛ ግን ዋጋው ይቀርበታል፤ ይሁን እንጂ እርሱ ራሱ፥ በእሳት ውስጥ አልፎ ሳይቃጠል እንደሚቀር ሰው ይድናል። 16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆናችሁንና የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ መኖሩን አታውቁምን? 17 እንግዲህ ሰው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው፤ ይህም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ። 18 ማንም ራሱን አያታል፤ በዚህ ዓለም የጥበብ ደረጃ ጥበበኛ መስሎ የሚታይ ቢኖር የእግዚአብሔርን እውነተኛ ጥበብ እንዲያገኝ ራሱን እንደ ሞኝ ይቊጠር። 19 የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ጥበበኞችን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። 20 እንዲሁም፥ “ጌታ የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ መሆኑን ያውቃል” የሚል ተጽፎአል። 21 ስለዚህ ሁሉ ነገር የእናንተ ስለ ሆነ ማንም በሰው አይመካ። 22 ጳውሎስም ቢሆን አጵሎስም ቢሆን፥ ጴጥሮስም ቢሆን፥ ዓለምም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ ሞትም ቢሆን፥ አሁን ያለውም ቢሆን፥ በኋላ የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉም የእናንተ ነው። 23 እናንተ ግን የክርስቶስ ልጆች ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። |