ሮሜ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በክርስቶስ ሐዲስ ሕይወት 1 ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው። 2 ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ። 3 በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን ዐስቡ እንጂ ትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር። 4 በአንዱ ሰውነታችን ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉ፥ ሥራቸውም ልዩ ልዩ እንደ ሆነ፥ 5 እንዲሁ ሁላችን ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው አካሎች ነን፤ ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፤ 6 እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን። ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር። 7 የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ፤ 8 የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛም በትጋት ይግዛ፤ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት። ስለ ልዩ ልዩ በጎ ምግባር 9 ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ 10 እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ መምህሮቻችሁንም አክብሩ። 11 ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ 12 በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ። 13 በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልንም አዘውትሩ። 14 የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። 15 ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ። 16 እርስ በርሳችሁም በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እና ዐዋቆች ነን አትበሉ። 17 ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ። 18 ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። 19 ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቍጣን አሳልፏት፥ “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራትን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአልና። 20 ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ። 21 ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው። |