ሚክያስ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ወቀሰ 1 እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ የሚናገረውን ስሙ፤ ተነሡ! ያላችሁን ቅርታ በተራሮች ፊት አቅርቡ! ኰረብቶችም የምትሉትን ይስሙ። 2 እናንተ ተራራዎች! እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ የሚያቀርበውን ወቀሳ ስሙ! እናንተም ጠንካራ የሆናችሁ የምድር መሠረቶች! አድምጡ! እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን ይወቅሳል ይገሥጻልም። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሕዝቤ ሆይ! ምን አደረግሁህ? ያከበድኩብህስ ነገር ምንድን ነው? እስቲ መልስልኝ። 4 ከግብጽ አወጣሁህ፤ ከባርነት ምድርም ታደግኹህ፤ ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን በፊትህ መሪዎች አድርጌ ሰጠሁህ። 5 ሕዝቤ ሆይ! የሞአብ ንጉሥ ባላቅ ምን እንደ ዐቀደብህና የቢዖር ልጅ በለዓም ምን እንደ መለሰለት አስታውስ፤ ከሺጢም ተነሥተህ ወደ ጌልጌላ በምትሄድበት ጊዜ በመንገድ ላይ የሆነውን ሁሉ አስታውስ፤ ይህን ሁሉ ብታስታውስ አንተን ለማዳን ያደረግኹትን ሁሉ ታውቃለህ።” እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው ነገር 6 ለኀያሉ አምላክ ለእግዚአብሔር ለመስገድ በምመጣበት ጊዜ ምን ይዤ ልቅረብ? ለእርሱ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ የአንድ ዓመት ጥጆችን ይዤ ልምጣን? 7 በሺህ የሚቈጠሩ አውራ በጎችን ወይም የዐሥር ሺህ ወንዞችን ውሃ የሚያኽል የወይራ ዘይት ባቀርብለት ይደሰት ይሆን? ስለ በደሌና ስለ ኃጢአቴ የበኲር ልጄን ልሠዋለትን? 8 እግዚአብሔር መልካም የሆነውንና ከአንተ የሚፈልገውን ነግሮሃል፤ ይኸውም ፍትሕን እንድትጠብቅ፥ ደግነትን እንድትወድ፥ ከአምላክህ ጋር በትሕትና እንድትመላለስ ነው። 9 እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ እርሱ ከተማይቱን እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በከተማይቱ የተሰበሰባችሁ ሰዎች አድምጡ! 10 ኃጢአተኛ በቤቱ በክፋት የሰበሰበውን ሀብትና የተረገመውን ሐሰተኛ ሚዛን ልረሳቸው እችላለሁን? 11 ታዲያ በሐሰተኛ ሚዛንና መስፈሪያ የሚጠቀሙትን ሰዎች እታገሣለሁን? 12 ሀብታሞቻችሁ በግፍ የተሞሉ ናቸው፤ የከተማይቱ ነዋሪዎችም ሐሰትን ይናገራሉ፤ በአንደበቶቻቸውም ይሸነግላሉ። 13 ስለዚህ በኃጢአታችሁ ምክንያት እናንተን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሥቼአለሁ። 14 ትበላላችሁ አትጠግቡም፤ ራቡም አይወገድላችሁም፤ ታግበሰብሳላችሁ እንጂ አይከማችላችሁም፤ ያጠራቀማችሁት ሀብት ቢኖርም በጦርነት አጠፋዋለሁ። 15 እህል ትዘራላችሁ ሰብል ግን አትሰበስቡም፤ የወይራ ፍሬ ትጨምቃላችሁ፤ ነገር ግን በዘይቱ አትጠቀሙም፤ የወይን ፍሬ ትጨምቃላችሁ፤ የወይን ጠጅ ግን አትጠጡም። 16 ይህ ሁሉ የሚደርስባችሁ የንጉሥ ዖምሪን ሥርዓት ስለ ጠበቃችሁና የንጉሥ አክዓብን አካሄድ ሁሉ ስለ ተከተላችሁ ነው፤ በእነርሱ ባህል ስለ ተመራችሁ አጠፋችኋለሁ፤ የከተማይቱን ነዋሪዎችም የሰው ሁሉ መሳቂያ አደርጋቸዋለሁ፤ በሕዝቤ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ እንድትሸከሙ አደርጋችኋለሁ።” |