ኢሳይያስ 59:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እጆቻችሁ በደም፥ ጣቶቻችሁም በበደል ተበክለዋል፤ አፋችሁ ውሸትን ይናገራል፤ በአንደበቶቻችሁም ታጒተመትማላችሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እጆቻችሁ በደም፣ ጣቶቻችሁ በበደል ተነክረዋል፤ ከንፈሮቻችሁ ሐሰትን ተናገሩ፤ ምላሶቻችሁ ክፉ ነገርን አሰሙ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፤ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እጃችሁ በደም ጣታችሁም በኀጢአት ተሞልትዋል፤ ከንፈራችሁም ዐመፅን ተናግሮአል፤ ምላሳችሁም ኀጢአትን አሰምቶአል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። |
“እጆቻችሁን ወደ እኔ ለጸሎት ብትዘረጉ፥ ወደ እናንተ አልመለከትም፤ እጆቻችሁ በደም የተበከሉ ስለ ሆኑ የቱንም ያኽል ልመና ብታበዙ አልሰማችሁም፤
ታማኝ የነበረችው ከተማ እንዴት እንደ አመንዝራ ሆነች! ቀድሞ ፍትሕ የሰፈነባትና የጻድቃን መኖሪያ ነበረች፤ አሁን ግን በነፍስ ገዳዮች የተሞላች ሆናለች።
“ከሞት ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ከሙታንም ዓለም ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል” እያላችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲሁም “ማታለልን እንደ መጠለያ፥ ሐሰትንም እንደ መጠጊያ አምባ ስላደረግን መቅሠፍት በሚመጣበት ጊዜ ሳይነካን ያልፋል” ብላችሁ ተስፋ ታደርጋላችሁ።
ኢየሩሳሌም ተሰናክላ በመንገዳገድ ላይ ናት፤ ይሁዳም ልትወድቅ ተቃርባለች፤ ምክንያቱም የሚናገሩትም ሆነ የሚሠሩት ሁሉ እግዚአብሔርን በመፈታተን ስለ ሆነ ክብሩን አቃለዋል።
ተቃጥሎ ዐመድ የሚሆነውን እንጨት እስከ ማምለክ ድረስ ሰው እንዴት ሞኝ ይሆናል? የሞኝነት አስተሳሰቡ አሳስቶታል፤ ራሱን ማዳን አይችልም፤ ወይም “ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም።” ብሎ መናገር አይችልም።
በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት በማጓደል ዐምፀናል፤ አምላካችንን ትተን ወደ ኋላ አፈግፍገናል፤ በልባችን ውስጥ ውሸትን አውጠንጥነን ስም በማጥፋትና በከሐዲነት ገልጠናቸዋል።
እኔም “እነሆ አንደበቶቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል የምኖር፥ አንደበቴም የረከሰብኝ ሰው ነኝ፤ ንጉሡን የሠራዊት አምላክን በዐይኖቼ አይቼአለሁና መጥፋቴ ስለ ሆነ ወዮልኝ!” አልኩ።
ልብሶችሽ በንጹሖችና በድኾች ደም ተበክለዋል። “ነገር ግን ይህን ሁሉ አድርገሽ፥ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ በእርግጥ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አይቈጣም!’ ትያለሽ፤ ነገር ግን ‘እኔ ኃጢአት አልሠራሁም’ ብለሽ በመካድሽ ምክንያት እኔ እግዚአብሔር እፈርድብሻለሁ።
ሕዝቤ እምነተ ቢሶችና አታላዮች ስለ ሆኑ፥ ከእነርሱ ተለይቼ በምድረ በዳ ውስጥ የምኖርበት የመንገደኞች ማደሪያ ቦታ ባገኝ፥ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!
ከዚህም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን ለማጥራት እንደ ብረት እፈትናቸዋለሁ፤ ሕዝቤ ክፉ ነገር ስለ ፈጸሙ ይህን ከማድረግ በቀር ሌላ ምን አደርጋቸዋለሁ?
ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ “ሐሰትን ስለ ተናገራችሁና ራእያችሁም ውሸት ስለ ሆነ እኔ በእናንተ ላይ እነሣለሁ። ይህንን የተናገርኩ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ነኝ።
“የሰው ልጅ ሆይ! በነፍሰ ገዳዮች የተሞላችውን ከተማ ልትፈርድባት ተዘጋጅተሃልን? እንግዲያውስ የፈጸመቻቸውን አጸያፊ ነገሮች ሁሉ ገልጠህ አሳያት።
ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ ለግድያ አዘጋጃችኋለሁ፤ ገዳይም ያሳድዳችኋል፤ ደም ማፍሰስን ስላልጠላችሁ ገዳይ ያሳድዳችኋል።
እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ እጅግ የከፋ ኃጢአት በመሥራት በድለዋል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ግድያ ፈጽመዋል፤ ከተማይቱንም በዐመፅ የተሞላች አድርገዋታል፤ ‘እግዚአብሔር አገራችንን ትቶአታል፤ እኛንም አይመለከተንም’ ይላሉ፤
“ከእኔ ርቀው ስለ ሄዱ ወዮላቸው! በእኔም ላይ ስለ ዐመፁ ጥፋት ይምጣባቸው፤ እኔ ልታደጋቸው ፈልጌ ነበር፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ።
እናንተም ተጨንቃችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትጮኹበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን እርሱ አይመልስላችሁም፤ ክፉ ሥራ ስለ ሠራችሁ ልመናችሁ አይሰማም።”
ከምድሪቱ ላይ ታማኝ ሰው ጠፍቶአል፤ አንድም ትክክለኛ ሰው የለም፤ ሁላቸውም ሰውን ለመግደል ያደባሉ፤ እርስ በርሳቸውም አንዱ ሌላውን ተከታትሎ ያጠምዳል።
እንዲህም ዐይነቱ ትምህርት የሚመነጨው በግብዝነት፥ ሐሰትን ሲናገሩ በጋለ ብረት እንደ ተተኮሰ ያኽል ሆኖ የደነዘዘ ኅሊናቸው ከማይወቅሳቸው ሰዎች ነው።