ሆሴዕ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር እስራኤልን መውቀሱ 1 በዚህች ምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እርሱ የሚልህን ሁሉ ስማ፦ “በምድሪቱ ላይ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርንም ማወቅ ጠፍቶአል። 2 በመሐላ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ይዋሻሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ያመነዝራሉም፤ ግፍና ግድያ እየበዛ ሄዶአል። 3 በዚህም ምክንያት በምድሪቱ ላይ ድርቅ ይመጣል፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ ይደክማሉ፤ እንስሶች፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ያልቃሉ።” እግዚአብሔር ካህናትን መውቀሱ 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምወቅሰው እናንተን ካህናትን ስለ ሆነ ሕዝቡን የሚከስ ወይም የሚወቀስ አይኑር። 5 እናንተ ካህናት ሆይ! በቀን ብርሃን ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ሌሊት ከእናንተ ጋር በጨለማ ይደናበራሉ፤ ስለዚህ እናት አገራችሁን አጠፋታለሁ። 6 ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ። 7 “እናንተ ካህናት ቊጥራችሁ በበዛ መጠን በደላችሁም በፊቴ እየበዛ ሄዶአል፤ ስለዚህ ክብራችሁን ገፍፌ አዋርዳችኋለሁ። 8 የሕዝቤ ኃጢአት ለእናንተ መበልጸጊያ በመሆኑ ሕዝቡ ኃጢአትን አብዝተው እንዲሠሩ ትፈልጋላችሁ። 9 እናንተ ካህናት እንደ ሕዝቡ ሆናችኋል፤ ስለዚህ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ቅጣት በእናንተም በካህናት ላይ ይደርሳል፤ የክፉ ሥራችሁንም ብድራት ትከፍላላችሁ። 10 ሕዝቤ እኔን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ፥ ይበላሉ አይጠግቡም፤ በአሕዛብ መስገጃ ቦታዎች ያመነዝራሉ፤ ግን ልጆችን አይወልዱም።” እግዚአብሔር ባዕድ አምልኮን መቃወሙ 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዝሙት ሥራ፥ የቈየና አዲስ የወይን ጠጅን መከተል የሕዝቤን አእምሮ አጥፍቶአል። 12 ስለዚህ ከእንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቁታል፤ የጥንቈላ ዘንጋቸውም ለጥያቄአቸው መልስ የሚሰጥ ይመስላቸዋል፤ በዝሙት መንፈስም ተመርተው ከእግዚአብሔር ርቀዋል። 13 በየተራራው ላይ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ በየኮረብታው ላይ ቊርባን ያቀርባሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ታላላቅ በሆኑና ቅርንጫፋቸው በተንሰራፋ ጥላቸው መልካም በሆነ ዋርካ፥ በለሳና ጥድ ሥር ነው። በዚህ ምክንያት ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ። ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። 14 ይሁን እንጂ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያት ምራቶቻችሁም አመንዝሮች ስለ ሆኑ አልቀጣቸውም፤ ምክንያቱም እናንተ ወንዶች ራሳችሁ በቤተ መቅደስ የሚሴስኑ ሴቶችን ተከትላችሁ ከእነርሱ ጋር ባዕድ አምልኮ ትፈጽማላችሁ፤ ስለዚህ ማስተዋል የጐደለው ሕዝብ ይጠፋል። 15 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እናንተ ብታመነዝሩም እንኳ የይሁዳ ሕዝብ በደለኛ እንዲሆን አታድርጉ፤ ወደ ጌልጌላ ወይም ወደ ቤትአዌን አትሂዱ፤ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁም አትማሉ። 16 የእስራኤል ሕዝብ እንደ እልኸኛ ጊደር እምቢተኞች ሆነዋል፤ ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን እንደ በግ ጠቦቶች በመልካም መስክ እንዴት ያሰማራቸዋል? 17 የእስራኤል ሕዝብ ከጣዖት አምልኮ ጋር ስለ ተጣመሩ ተዉአቸው የፈለጉትን ያድርጉ። 18 ብዙ የወይን ጠጅ ከጠጡ በኋላ የዝሙት ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ አለቆቻቸውም አሳፋሪ ነገሮችን ማድረግ አጥብቀው ይወዳሉ። 19 እነርሱም በነፋስ ተጠርገው የሚወሰዱትን ያኽል ርቀው ይሄዳሉ፤ ለጣዖት በመሠዋታቸውም ያፍራሉ። |