Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሚክያስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሚክያስ የእስራኤልን መሪዎች መገሠጹ

1 ከዚህም በኋላ እንዲህ አልኳቸው፦ “የእስራኤል ሕዝብ ልጆች መሪዎችና የእስራኤል ሕዝብ ገዢዎች! አድምጡ! ትክክለኛ ፍርድን ማወቅ ይገባችሁ አልነበረምን?

2 እናንተ ግን መልካሙን ጠልታችሁ ክፉውን ወደዳችሁ፤ ሕዝቤን በቊመናቸው ቆዳቸውን ገፈፋችሁ፤ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያችሁ፤

3 የሕዝቤን ቆዳ ገፋችሁ አጥንታቸውን ቈራርጣችሁ ለአፍላልና ለድስት እንደሚቈራረጥ ሥጋ አደረጋችኋቸው፤ ሥጋቸውንም በላችሁ።

4 እናንተም ተጨንቃችሁ ወደ እግዚአብሔር የምትጮኹበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን እርሱ አይመልስላችሁም፤ ክፉ ሥራ ስለ ሠራችሁ ልመናችሁ አይሰማም።”

5 እግዚአብሔር ስለ ሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ይላል፦ “ጥቅም የሚያገኙበት ሲሆን ‘ሰላም ይወርድላችኋል’ እያሉ ይሰብካሉ፤ ጥቅም በማያገኙበት ጊዜ ‘ጦርነት ይመጣባችኋል’ እያሉ በማወጅ ሕዝቡን ያስታሉ፤

6 ስለዚህ ራእይ የማያዩበት ሌሊት ይመጣባቸዋል፤ የማይገለጥላቸውም ጨለማ ሆኖባቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራእይ አያዩም፥ ትንቢትም አይናገሩም።

7 ‘ራእይ እናያለን፥ ትንቢት እንናገራለን’ የሚሉ ሁሉ ስለማይሳካላቸው ይዋረዳሉ፤ እግዚአብሔርም መልስ ስለማይሰጣቸው ከማፈራቸው የተነሣ ፊታቸውን በእጃቸው ሸፍነው ይሄዳሉ።”

8 እኔን ግን እግዚአብሔር በመንፈሱና በኀይሉ ሞልቶኛል፤ የእስራኤል ሕዝብ በደላቸውና ኃጢአታቸው ምን እንደ ሆነ አስታውቃቸው ዘንድ በግልጽ ትክክለኛ ፍርድን ለመስጠት ብርታትን ሰጥቶኛል።

9 እናንተ ፍትሕን የምትጸየፉና ትክክለኛውን ነገር ሁሉ የምታጣምሙ የያዕቆብ ልጆች መሪዎች፥ የእስራኤል ሕዝብ አለቆች ይህን ስሙ፤

10 እናንተ ደም በማፍሰስ ጽዮንን፥ በደል በመሥራት ኢየሩሳሌምን የምትገነቡ ናችሁ።

11 የከተማይቱም ሹማምንት የሚፈርዱት በጉቦ ነው፤ ካህናቱ ያለ ዋጋ አያስተምሩም፤ ነቢያቱም ያለ ገንዘብ ትንቢት አይናገሩም፤ ይህም ሁሉ ሆኖ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለ ሆነ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይመጣብንም” በማለት በእግዚአብሔር ይመካሉ።

12 ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ ማሳ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ ቤተ መቅደሱም የተሠራበት ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ይሆናል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos