ኤርምያስ 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኤርምያስ ለይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ የተናገረው ቃል 1-2 እግዚአብሔር የዳዊት ዘር ወደ ሆነው ወደ ይሁዳ ቤተ መንግሥት እንድወርድና በዚያም ለንጉሡ፥ ለመኳንንቱና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እኔ የምነግራቸውን ቃል እንዲያዳምጡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለኝ፦ 3 “እኔ እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድና እውነት የሆነውን ነገር እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ አንዱ ሌላውን በመቀማት ግፍ እንዳይሠራ ጠብቁ፤ መጻተኞችን፥ እናትና አባት የሞቱባቸውን ልጆችና፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በመጨቈን አታንገላቱ፤ በዚህም በተቀደሰ ስፍራ የንጹሕ ሰው ደም አታፍስሱበት። 4 ልክ እኔ እንዳዘዝኳቸው ብታደርጉ፥ የዳዊት ዘሮች ከዙፋናቸው አይወርዱም፤ እንደ ወትሮው ሁሉ ከመኳንንቱና ከሕዝቡ ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ላይ በመቀመጥ በዚህ ቤተ መንግሥት የቅጽር በሮች መግባት ትችላላችሁ። 5 ትእዛዜን የማትፈጽሙ ከሆነ ግን ይህ ቤተ መቅደስ ፈራርሶ እንደሚወድቅ በራሴ በመማል አረጋግጥላችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 6 “የይሁዳ ነገሥታት ቤተ መንግሥት የገለዓድን አገርና የሊባኖስን ተራራዎች ያኽል ለእኔ የተዋበ ነው፤ ነገር ግን ማንም የማይኖርበት ባድማ አደርገዋለሁ። 7 እርሱን የሚያፈራርሱ ሰዎችን እልካለሁ፤ እነርሱም መጥረቢያቸውን ይዘው ይመጣሉ፤ ከተዋበ የሊባኖስ ዛፍ የተሠሩትንም ዐምዶች ቈራርጠው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል። 8 “ከዚያን በኋላ በዚያ በኩል የሚያልፉ ብዙ የውጪ አገር ሰዎች ‘በዚህች በታላቅ ከተማ ላይ እግዚአብሔር ይህን ጥፋት ያመጣው ለምን ይሆን?’ በማለት እርስ በርሳቸው ይጠያየቃሉ። 9 እናንተ ከእኔ ከአምላካችሁ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችሁ ባዕዳን አማልክትን በማምለካችሁና በማገልገላችሁ ምክንያት መሆኑንም ይረዳሉ።” ኤርምያስ ስለ ሻሉም የተናገረው ቃል 10 የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ስለ ንጉሥ ኢዮስያስ አታልቅሱ፤ በመሞቱም አትዘኑ፤ ነገር ግን የኢዮስያስ ልጅ ሻሉም፤ ዳግመኛ ወደማይመለስበት ቦታ ስለሚወሰድ፥ የትውልድ አገሩንም ዳግመኛ ስለማያይ፥ ለእርሱ ምርር ብላችሁ አልቅሱ። 11 በአባቱ ምትክ በይሁዳ ስለ ነገሠው ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሻሉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዳግመኛ ወደማይመለስበት ወደ ሩቅ አገር ይሄዳል፤ 12 በዚያም ተማርኮ በተወሰደበት አገር ስለሚሞት ዳግመኛ ተመልሶ ይህችን ምድር አያይም።” ኤርምያስ ስለ ንጉሥ ኢዮአቄም የተናገረው ቃል 13 ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዐመፅ ለሠራተኞች የድካማቸውን ዋጋ ሳይከፍል ለሚያሠራ ሰው ወዮለት! 14 ይህ ሰው “ለራሴ ትልቅ ቤት ከሰፊ ሰገነት ጋር እሠራለሁ፤ እንዲሁም ሰፋፊ መስኮቶችን አወጣለታለሁ፤ ቤቱን በሰፋፊ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት አስጌጠዋለሁ፤ ደማቅ ቀይ ቀለምም እቀባዋለሁ” ይላል። 15 ሌሎች ሰዎች ከሚያደርጉት ይበልጥ ምርጥ በሆነ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤትህን በመሥራትህ የተሻልክ ንጉሥ የሆንክ ይመስልሃልን? አባትህ ደስታ የሞላበት ሙሉ ዕድሜ ነበረው፤ እርሱ ዘወትር ትክክለኛና ቅን ከመሆኑ የተነሣ የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር። 16 ለድኾች በቅንነት ስለሚፈርድ፥ ሁሉ ነገር ይሳካለት ነበር፤ እግዚአብሔርን ማወቅ ይሉሃል ይህ ነው። 17 የአንተ ሥራ ንጹሕ ደምን ማፍሰስና ሰውን መጨቈን ነው፤ ዐይንህና ልብህም የሚያተኲሩት አጭበርብሮ ትርፍን በማግበስበስ ላይ ብቻ ነው። 18 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም የሚለው ይህ ነው፥ “እርሱ በሚሞትበት ጊዜ ‘ዋይ! ወዮ! ወንድሜ ሆይ!’ እያሉ በማልቀስ አያዝኑለትም፤ እንዲሁም ‘ጌታዬ ሆይ! ንጉሤ ሆይ! ወዮ!’ እያለ የሚያለቅስለት አይኖርም። 19 ሬሳውም ክብር አጥቶ እየተጐተተ፥ ከኢየሩሳሌም ቅጽር በር ውጪ ተጥሎ የአህያ አቀባበር ይቀበራል።” ኢየሩሳሌም ስለሚገጥማት ችግር ኤርምያስ የተናገረው ቃል 20 የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የጦር ጓደኞቻችሁ ሁሉ ስለ ተሸነፉ ወደ ሊባኖስ ሂዱና ጩኹ፤ ወደ ባሳን ምድርም ሄዳችሁ አልቅሱ፤ በሞአብ ተራራዎች ላይ ሆናችሁም ተጣሩ። 21 በብልጽግና በምትኖሩበት ጊዜ እግዚአብሔር ተናገራችሁ፤ እናንተ ግን ማዳመጥ እምቢ አላችሁ፤ ከመጀመሪያ ጀምሮ የምታደርጉት ይህንኑ ነው። እግዚአብሔርንም መታዘዝ እምቢ አላችሁ። 22 በምትሠሩት ኃጢአት ምክንያት ነፋስ ገለባን ጠራርጎ እንደሚወስድ፥ መሪዎቻችሁ ተጠራርገው ይወሰዳሉ። የተማመናችሁባቸው የጦር ጓደኞቻችሁም ተማርከው ወደ ባዕድ ሀገር ይወሰዳሉ፤ ኀፍረትና ውርደትም ይደርስባችኋል። 23 አሁንማ ከሊባኖስ መጥቶ በተሠራ የሊባኖስ እንጨት ውስጥ በሰላም ዐርፋችሁ ትኖራላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ወላድ ሴት የምጥ ጣዕር ሲይዛችሁ ምን ይበጃችሁ ይሆን? በዮአኪን ላይ የደረሰ የእግዚአብሔር ፍርድ 24 ለኢዮአቄም ልጅ ለኢኮንያን እግዚአብሔር እንዲህ አለው፦ “እኔ ሕያው አምላክ አንተ በቀኝ እጄ እንደሚገኝ የማኅተም ቀለበት ብትሆን እንኳ አውልቄ እጥልሃለሁ፤ 25 ሊገድሉህ ለሚፈልጉና አንተም እጅግ ለምትፈራቸው ሕዝብ፥ ማለትም ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ለባቢሎናውያን አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ 26 አንተንም፥ የወለደችህ እናትህንም እንድትሰደዱ አደርጋለሁ፤ ማንኛችሁም ወዳልተወለዳችሁበት አገር ሄዳችሁ ሁላችሁም እዚያ ትሞታላችሁ። 27 ይህችን አገር እንደገና ለማየት ትናፍቃለህ፤ ነገር ግን ዳግመኛ አትመለስባትም።” 28 እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ንጉሥ ኢኮንያን ከተጣለ በኋላ ማንም እንደማይፈልገው ሰባራ ገንቦ መሆኑ ነውን? እርሱና ልጆቹ ተማርከው ወደማያውቁት አገር የተወሰዱት ለምንድን ነው?” 29 ምድር፥ ምድር፥ ምድር ሆይ! እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እነሆ አድምጪ! 30 “ይህ ሰው ልጆቹን ሁሉ አጥቶ ኑሮው የማይሳካለት እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ የዳዊትን ዙፋን ለመውረስ በይሁዳ የሚነግሡ ዘሮች አይተርፉለትም ብለሽ መዝግቢ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |