ሆሴዕ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “ሕዝቤን እስራኤልን ለመፈወስና እንደገናም እንዲበለጽጉ ለማድረግ በፈለግሁ ጊዜ የሕዝቡ በደልና የሰማርያ ክፋት ጐልቶ ይታያል፤ እርስ በርሳቸው ሐሰት ይናገራሉ፤ ቤት እየሰበሩ ይሰርቃሉ፤ በቡድን በቡድን ሆነው በየመንገዱ ይዘርፋሉ። 2 ነገር ግን እኔ ይህን ሁሉ ክፋታቸውን እንደማስታውስ ከቶ አይገነዘቡም፤ ከዚህ የተነሣ በገዛ ኃጢአታቸው ተከበዋል፤ ክፉ ሥራቸው ሁሉ ከእኔ የተሰወረ አይደለም።” በቤተ መንግሥት የተደረገ ሤራ 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ንጉሡን በክፋታቸው፥ መኳንንቱን በውሸታቸው ያስደስታሉ። 4 ሁሉ ዘማውያን ናቸው፤ ሊጡ እስኪቦካለት ድረስ ዳቦ ጋጋሪው እሳቱን መቈስቈስ እንደማያስፈልገው እንደ ጋለ ምድጃ ናቸው። 5 በንጉሣቸው ክብረ በዓል ቀን መኳንንቱ ብዙ የወይን ጠጅ በመጠጣት ሰክረው ታመሙ፤ ጋጋሪውም ለሚያፌዙ ሰዎች ምልክት ለመስጠት እጁን ዘረጋ። 6 ሤራ ለመጐንጐን ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤ ቊጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ሲጤስ ያድራል፤ ሲነጋ ግን እንደሚነድ እሳት ይንበለበላል። 7 “ሁሉም በቊጣ እንደ ምድጃ ግለው ገዢዎቻቸውን ፈጁ፤ ንጉሦቻቸውንም በየተራ አጠፉ፤ ይህም ሁሉ ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ የእኔን ርዳታ የጠየቀ የለም።” የእስራኤል ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር መደባለቃቸው 8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቁ፤ በዚህም ምክንያት እነርሱ እንዳልተገለበጠ ቂጣ የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ 9 ባዕዳን ጒልበታቸውን በዘበዙት፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም፤ ሽበት ጣል ጣል አድርጎባቸዋል፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም። 10 የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕታቸው በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ወደ እኔ ወደ አምላካቸው አልተመለሱም ከቶም አልፈለጉኝም። 11 የእስራኤል ሕዝብ እንደ ርግብ የዋህና አእምሮ የጐደላቸው ሆነዋል፤ ስለዚህም ርዳታ ለማግኘት አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራሉ፤ አንድ ጊዜም ወደ አሦር ይበራሉ። 12 በሚዘዋወሩበት ቦታ ሁሉ ወጥመዴን ዘርግቼ እንደ ወፍ እይዛቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ እቀጣቸዋለሁ። 13 “ከእኔ ርቀው ስለ ሄዱ ወዮላቸው! በእኔም ላይ ስለ ዐመፁ ጥፋት ይምጣባቸው፤ እኔ ልታደጋቸው ፈልጌ ነበር፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ። 14 በአልጋቸው ላይ ተጋድመው ይጮኻሉ እንጂ ከልባቸው ወደ እኔ አይጸልዩም፤ እህልና የወይን ጠጅ ለማግኘት ሰውነታቸውን ይተለትላሉ፤ በእኔም ላይ ያምፃሉ። 15 ያሠለጠንኳቸውና ጒልበታቸው አንዲጠነክር ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ያሤራሉ፤ 16 ከእኔ ርቀው ወደ ከንቱ አምልኮ ተመለሱ፤ ዓላማውን እንደሚስት እንደ ተበላሸ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ክፉ ነገርን ከመናገራቸው የተነሣ በሰይፍ ተመተው ይሞታሉ፤ በግብጻውያንም ዘንድ መዘባበቻ ይሆናሉ።” |