ማቴዎስ 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ ( ማር. 15፥1 ፤ ሉቃ. 23፥1-2 ፤ ዮሐ. 18፥28-32 ) 1 ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ ተማከሩ። 2 ከዚህ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱና ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። 3 ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት መልሶ ሰጣቸው፤ 4 “ንጹሑን ሰው ለሞት አሳልፌ በመስጠቴ በድዬአለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ፥ እኛ ምን ቸገረን! የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት። 5 እርሱም ሠላሳውን ጥሬ ብር በቤተ መቅደስ ውስጥ በትኖ፥ ትቶአቸው ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። 6 የካህናት አለቆች ሠላሳውን ጥሬ ብር አንሥተው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለ ሆነ ከቤተ መቅደስ መባ ጋር ልንቀላቅለው አይፈቀድም” አሉ። 7 ስለዚህ ከተመካከሩ በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። 8 በዚህ ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” እየተባለ ይጠራል። 9 በዚህ ሁኔታ “የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ለእርሱ ዋጋ የሚሆን ሠላሳ ጥሬ ብር ወሰዱ፤ 10 ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት” ተብሎ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ። ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መቅረቡ ( ማር. 15፥2-5 ፤ ሉቃ. 23፥3-5 ፤ ዮሐ. 18፥33-38 ) 11 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” ሲል መለሰ። 12 ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲወነጅሉት ምንም መልስ አልሰጠም። 13 ከዚህ በኋላ ጲላጦስ “በስንት ነገር ሲወነጅሉህ አትሰማምን?” አለው። 14 ኢየሱስ ግን ገዢው እስኪደነቅ ድረስ ለአንዲት ክስ እንኳ ቃል አልመለሰለትም። ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ( ማር. 15፥6-15 ፤ ሉቃ. 23፥13-25 ፤ ዮሐ. 18፥39-40 ፤ 19፥1-16 ) 15 ገዢው በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሕዝቡ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ፈቶ መልቀቅ አስለምዶ ነበር። 16 በዚያን ጊዜ “በርባን” የተባለ በዓመፀኛነቱ የታወቀ እስረኛ ነበረ። 17 ስለዚህ ሰዎቹ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ፥ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ነውን ወይስ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን?” ሲል ጠየቃቸው። 18 ይህን ያለበት ምክንያት ኢየሱስን በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ስለ ነበር ነው። 19 ከዚህም በላይ ጲላጦስ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ ሌሊት በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ በንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። 20 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች “በርባን ይለቀቅ! ኢየሱስ ይገደል!” ብለው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አግባቡ። 21 ገዢውም “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ሕዝቡን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “በርባንን እንድትፈታልን እንፈልጋለን” ሲሉ መለሱ። 22 ጲላጦስም “ታዲያ፥ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!” ሲሉ መለሱ። 23 ገዢውም ለምን? “እርሱ ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። 24 ስለዚህ ጲላጦስ ይህ ነገር ሁከት እንደሚያስነሣ እንጂ ሌላ ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ ውሃ አስመጥቶ “እኔ ለዚህ ሰው ሞት ኀላፊ አይደለሁም፤ ኀላፊነቱ የእናንተ ነው!” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። 25 ሕዝቡም ሁሉ “በእርሱ ሞት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ። 26 በዚያን ጊዜ ጲላጦስ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። የወታደሮቹ በኢየሱስ ላይ ማፌዝ ( ማር. 15፥16-20 ፤ ዮሐ. 19፥2-3 ) 27 በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ወታደሮቹንም ሁሉ በኢየሱስ ዙሪያ ሰበሰቡ። 28 ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት። 29 የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት፤ በፊቱም እየተንበረከኩ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ 30 ምራቃቸውንም ይተፉበት ነበር፤ ዘንጉንም ከእጁ ወስደው ራስ ራሱን ይመቱት ነበር። 31 ካፌዙበት በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ። የኢየሱስ መሰቀል ( ማር. 15፥21-32 ፤ ሉቃ. 23፥26-43 ፤ ዮሐ. 19፥17-27 ) 32 ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። 33 ከዚህ በኋላ ትርጒሙ “የራስ ቅል” ወደ ሆነው ወደ ጎልጎታ ደረሱ። 34 በዚያም ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ለኢየሱስ አቀረቡለት፤ እርሱ ግን ቀመስ አድርጎ ሊጠጣው አልፈለገም። 35 ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። 36 በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37 የተከሰሰበትንም ወንጀል የሚያመለክት፥ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው?” የሚል ጽሑፍ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖሩ። 38 በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ። 39 በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች በንቀት ራሳቸውን እየነቀነቁ፥ 40 “አንተ ቤተ መቅደስን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከመስቀል ውረድ!” በማለት ያላግጡበት ነበር። 41 በዚሁም ዓይነት የካህናት አለቆች ከሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ 42 “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንመንበት! 43 እርሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው!” 44 እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር። የኢየሱስ ሞት ( ማር. 15፥33-41 ፤ ሉቃ. 23፥44-49 ፤ ዮሐ. 19፥28-30 ) 45 ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። 46 ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። 47 በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። 48 በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። 49 ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። 50 ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። 51 በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ 52 መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። 53 ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። 54 የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ። 55 በሩቅ ሆነው የሚመለከቱት ብዙ ሴቶችም በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ ከገሊላ ጀምረው ኢየሱስን እያገለገሉ ይከተሉት የነበሩ ናቸው። 56 ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙባቸው ነበር። የኢየሱስ መቀበር ( ማር. 15፥42-47 ፤ ሉቃ. 23፥50-56 ፤ ዮሐ. 19፥38-42 ) 57 በመሸ ጊዜ ዮሴፍ የሚባል አንድ የአርማትያስ ከተማ ሀብታም ሰው ወደዚያ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ 58 ይህ ሰው፥ ወደ ጲላጦስ ሄደና የኢየሱስን አስከሬን ለመነ፤ ጲላጦስም አስከሬኑ እንዲሰጠው አዘዘ። 59 ስለዚህ ዮሴፍ አስከሬኑን አውርዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው። 60 ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ከዚህ በኋላ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘጋና ሄደ። 61 መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም፥ እዚያ በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር። 62 በማግስቱ ቅዳሜ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን በአንድነት ወደ ጲላጦስ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ 63 “ጌታ ሆይ! ያ አሳሳች ገና በሕይወቱ ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት እነሣለሁ’ ያለው ትዝ አለን። 64 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡም ‘እነሆ፥ ከሞት ተነሥቶአል’ እንዳይሉ መቃብሩ እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ አለበለዚያ የኋለኛው ማሳሳት ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።” 65 ጲላጦስም “እነሆ፥ የሚጠብቁ ወታደሮች አሉአችሁ፤ ሂዱና በምታውቁት ዐይነት አስጠብቁ” አላቸው። 66 ስለዚህ ሄደው ድንጋዩን በማኅተም አሸጉና መቃብሩን በወታደሮች አስጠበቁ። |