ገላትያ 2:20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተሰቀልኩ ያኽል ስለምቈጥር ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቶስ በእኔ ውስጥ ይኖራል እንጂ እኔ ለራሴ ሕይወት የምኖር አይደለሁም፤ አሁንም በሥጋዊ አካሌ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በማመን በተገኘው ሕይወት ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። |
እኔም የምለምነው ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ እንዲሁም አባት ሆይ! አንተ በእኔ እንዳለህ፥ እኔም በአንተ እንዳለሁ፥ እነርሱም በእኛ እንዲኖሩ ነው፤ አንተ እንደ ላክኸኝም ዓለም እንዲያምን ነው።
ጻድቅ በእምነት ሕይወትን ያገኛል ተብሎ ተጽፎአል፤ የእግዚአብሔር ጽድቅም በሥራ ስለ ታየ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሰው የሚጸድቀው በእምነት ነው።
ወደዚህ አሁን በእምነት ጸንተን ወደምንገኝበት ጸጋ የገባነው በእርሱ ስለ ሆነ በተስፋ የእግዚአብሔር ክብር ተካፋዮች በመሆናችን እንመካለን።
ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ያስረዳል።
እንዲሁም የሰውነታችሁን ክፍሎች የዐመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታስገዙ፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥታችሁ ሕያዋን እንደ ሆናችሁ በማድረግ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች ሁሉ የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አስገዙ።
እናንተ በእኔ ዐድሮ የሚናገረው ክርስቶስ መሆኑን ለማረጋገጥ ትፈልጋላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ የሚታየውም የእርሱ ኀይል ነው እንጂ ድካሙ አይደለም።
በእምነታችሁ የጸናችሁ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጣችሁ መሆኑን አልተገነዘባችሁምን? አለበለዚያ በፈተና ወድቃችኋል ማለት ነው፤
በሕይወት ያሉት ሁሉ ለእነርሱ ለሞተውና ከሞትም ለተነሣው እንዲኖሩ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ለራሳቸው ሲሉ እንዳይኖሩ ክርስቶስ ለሁሉም ሞተ።
ነገር ግን ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ ሕግን በመፈጸም እንዳልሆነ እናውቃለን፤ እኛም ሕግን በመፈጸም ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ማንም ሰው የኦሪትን ሕግ በመፈጸም አይጸድቅም።
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ መመካት ከእኔ ይራቅ፤ በዚህም መስቀል ዓለም ከእኔ ተለይቶአል፤ እኔም ከዓለም ተለይቼአለሁ።
ክርስቶስ እንደ ወደደንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም መዓዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ኑሩ።
እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ ሊገልጥላቸው የፈቀደው ያለውን የዚህን ምሥጢር የክብር ብልጽግና በእናንተ በአሕዛብ መካከል ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው።
እንዲሁም እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣውን፥ ከሚመጣው ቊጣ የሚያድነንን፥ የልጁን የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት እንዴት እንደምትጠባበቁም ይመሰክራሉ።
ክርስቶስ ከዐመፃ ሁሉ ሊያድነንና መልካም ሥራ ለመሥራት ትጉሆችና ለእርሱ የተለየን ንጹሕ ሕዝብ እንድንሆን ያነጻን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።
ኢየሱስ ክርስቶስን ያላያችሁት እንኳ ብትሆኑ ትወዱታላችሁ፤ አሁን እንኳ የማታዩት ብትሆኑ ታምኑበታላችሁ፤ በቃላት ሊገለጥ በማይቻልና በከበረ ደስታ ደስ ይላችኋል።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንኖር እርስ በርሳችን አንድነት ይኖረናል። ደግሞም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።
እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፤