Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


2 ቆሮንቶስ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጳውሎስና ሐሰተኞች ሐዋርያት

1 ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እባካችሁ ታገሡኝ።

2 እንደ አንዲት ንጽሕት ልጃገረድ በድንግልናዋ ለአንድ ባል እንደምትታጭ እኔም እናንተን ለክርስቶስ ስላአጨኋችሁ ስለ እናንተ መንፈሳዊ ቅናት እቀናለሁ።

3 እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ሐሳብ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ያላችሁን ቅንና ንጹሕ የሆነ ታማኝነት ትተዋላችሁ ብዬ እፈራለሁ።

4 አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ የሰበክነውን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም እናንተ የተቀበላችሁትን መንፈስ ሳይሆን ሌላ መንፈስ ብትቀበሉ፥ ወይም የተቀበላችሁትን ወንጌል ሳይሆን ሌላ ወንጌል ብትቀበሉ፥ ዝም ብላችሁ ተሸነፋችሁ ማለት ነው።

5 ነገር ግን እኔ ከነዚህ ታላላቅ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም።

6 በአነጋገር ፈሊጥ ምሁር ባልሆንም እንኳ ዕውቀት አይጐድለኝም፤ ይህንንም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ በግልጥ አስረድተናችኋል።

7 እኔ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ለእናንተ መስበኬና እናንተን ከፍ ለማድረግ ራሴን ማዋረዴ ምናልባት እንደ ኃጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን?

8 እናንተን ለማገልገል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ።

9 ከእናንተ ጋር ሳለሁ ችግር በደረሰብኝ ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ይረዱኝ ስለ ነበር በማንም ሸክም አልሆንኩም፤ እስከ አሁን በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም አልሆንኩም፤ ለወደፊትም ሸክም አልሆንባችሁም።

10 የክርስቶስ እውነት በእኔ ውስጥ በመኖሩ እንዳልመካ የሚያደርገኝ በአካይያ አገሮች ማንም የለም።

11 ምክንያቱስ ምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነውን? እንደምወዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል።

12 እነዚያ ሌሎች ሐዋርያት “እኛም እንደ እነርሱ እንሠራለን” እያሉ የሚመኩበትን ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደፊትም ደግሞ አደርጋለሁ።

13 እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው።

14 ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ሰይጣን እንኳ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለውጣል።

15 ስለዚህ እነዚህ የሰይጣን አገልጋዮች የጽድቅ አገልጋዮችን ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ አያስደንቅም፤ በመጨረሻ የሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።


ጳውሎስ በሐዋርያነቱ ምክንያት የደረሰበት መከራ

16 “ማንም ሰው እኔ ሞኝ የሆንኩ አይምሰለው” ብዬ እንደገና እናገራለሁ። ሞኝ ብመስላችሁም እንኳ ጥቂት እንድመካ እንደ ሞኝ አድርጋችሁ ቊጠሩኝ።

17 እንደዚሁ በትምክሕት ስናገር የምናገረው እንደ ጌታ ፈቃድ ሳይሆን እንደ ሞኝ ሆኜ ነው።

18 ብዙዎች በሥጋዊ ነገር ስለሚመኩ እኔም እመካለሁ።

19 እናንተ አስተዋዮች እንደ መሆናችሁ መጠን ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ።

20 እንዲሁም ማንም እንደ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበዘብዛችሁ፥ ማንም ቢጠቀምባችሁ፥ ማንም ቢንቃችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።

21 የሚያሳፍረኝ ቢሆንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ብርቱዎች አለመሆናችንን እገልጥላችኋለሁ፤ ነገር ግን ማንም ለመመካት ቢደፍር እኔም እንደ እርሱ ደፍሬ እመካለሁ፤ ይህን የምለው አሁንም እንደ ሞኝ ሆኜ ነው።

22 እነርሱ ዕብራውያን ናቸውን? እኔም ዕብራዊ ነኝ፤ እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውን? እኔም እስራኤላዊ ነኝ፤ እነርሱ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም የአብርሃም ዘር ነኝ።

23 እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እኔ ከእነርሱ ይበልጥ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ፤ ይህንንም ስል እንደ እብድ ሆኜ ነው የምናገረው፤ ከእነርሱ ይበልጥ ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት አደጋ ደርሼአለሁ፤

24 ሠላሳ ዘጠኝ፥ ሠላሳ ዘጠኝ ጅራፍ አምስት ጊዜ በአይሁድ ተገርፌአለሁ፤

25 ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በባሕር ላይ ነበርኩ፤

26 በጒዞዬ ብዛት የወንዝና የጐርፍ፥ የሽፍቶችም አደጋ ደርሶብኛል፤ ከአይሁድ ወገኖቼና ከአሕዛብ አደጋ ደርሶብኛል፤ በከተማና በበረሓ በባሕርም አደጋ ደርሶብኛል፤ እንዲሁም ከሐሰተኞች አማኞች አደጋ ደርሶብኛል።

27 ብዙ ሥራና ድካም ነበረብኝ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ በራብና በውሃ ጥም ተጨንቄአለሁ፤ ብዙ ጊዜም የምግብ እጦት ደርሶብኛል፤ ብርድና መራቆትም ደርሶብኛል።

28 ሌላውንም ሁሉ ነገር ሳልቈጥር ስለ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ በየቀኑ በማሰብ እጨነቅ ነበር።

29 አንድ ሰው ሲደክም እኔ አብሬው ያልደከምኩት መቼ ነው? አንድ ሰው በኃጢአት ሲሰናከል እኔም ያልተናደድኩት መቼ ነው?

30 መመካት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ የምመካው ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች ነው።

31 ለዘለዓለም የተመሰገነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር እንደማልዋሽ ያውቃል።

32 በደማስቆ ከተማ በነበርኩበት ጊዜ ከንጉሡ ከአሬታስ በታች የነበረው አገረ ገዥ እኔን ለመያዝ ፈልጎ የከተማውን በሮች በዘበኞች ያስጠብቅ ነበር።

33 ነገር ግን ሰዎች በቅጥሩ መስኮት በኩል በቅርጫት አድርገው አወረዱኝና ከእጁ አመለጥኩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos