ፊልጵስዩስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ከተማ ለሚኖሩ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፥ እንዲሁም ለኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት፦ 2 ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። የጳውሎስ የምስጋና ጸሎት 3 እናንተን በማስታውስበት ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 4 ስለ ሁላችሁም በምጸልይበት ጊዜ ሁሉ ጸሎቴ በደስታ የተሞላ ነው። 5 ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስከ አሁን ወንጌልን በመስበክ የሥራዬ ተባባሪዎች ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 6 ይህን መልካም ሥራ በእናንተ ሕይወት ውስጥ የጀመረ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመለስበት ቀን ወደ ፍጻሜ እንደሚያደርሰው እርግጠኛ ነኝ። 7 አሁን በእስር ቤት ባለሁበት ጊዜና ከመታሰሬም በፊት ለወንጌል እውነት ለመከላከልና እርሱንም ለማጽናት እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዕድል ሁላችሁም ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ እናንተ ሁልጊዜ በልቤ ናችሁ። ስለዚህም ስለ እናንተ የሚሰማኝ ስሜት ትክክል ነው። 8 በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያኽል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 9 ፍቅራችሁ ዕውቀትና ማስተዋል የሞላበት ሆኖ እያደገ እንዲሄድ እጸልያለሁ። 10 ይኸውም የተሻለውን ነገር መርምራችሁ እንድታውቁና ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ንጹሖችና ነውር የሌለባችሁ ሆናችሁ እንድትገኙ ነው። 11 በዚህም ዐይነት ሕይወታችሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ የተሞላ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የምታስገኙ ትሆናላችሁ። የጳውሎስ መታሰር ለወንጌል መስፋፋት እንደ ረዳ 12 ወንድሞቼ ሆይ! በእኔ ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ወንጌል በይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንድታውቁ እወዳለሁ። 13 እኔም የታሰርኩት በክርስቶስ ምክንያት መሆኑን የቤተ መንግሥት ዘበኞችና ሌሎችም እዚያ ያሉት ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ። 14 በእኔ መታሰር ምክንያት ከአማኞች ወንድሞች ብዙዎቹ በይበልጥ በጌታ የሚተማመኑ ሆነዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሀት ለማብሠር ከቀድሞ የበለጠ ድፍረት አግኝተዋል። 15 ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የክርስቶስን የምሥራች ቃል የሚያበሥሩት በቅናት፥ ሌሎቹም በፉክክር መንፈስ ነው፤ ሌሎቹ ግን ክርስቶስን የሚሰብኩት በቅን ልቡና ነው። 16 እነዚህ የእግዚአብሔርን ቃል በቅን ልቡና የሚያበሥሩት ከፍቅር የተነሣ ነው፤ እነርሱም እኔ ለወንጌል ለመከላከል እዚህ የተጣልኩ መሆኔን ስለሚያውቁ ነው። 17 እነዚያ ግን ስለ ክርስቶስ አጣምመው የሚሰብኩት በቅንነት ሳይሆን በራስ ወዳድነትና በእስራቴ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊያመጡብኝ አስበው ነው። 18 ያም ሆነ ይህ በዚህ ደስ ይለኛል፤ በማስመሰልም ሆነ በእውነት በሁሉም መንገድ ክርስቶስ ይሰበካል። 19 ሌላው የምደሰትበት ምክንያት በእናንተ ጸሎትና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ርዳታ ነጻ እንደምወጣ ስለማውቅ ነው። 20 በፍጹም እንደማላፍር በተስፋ እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን ዘወትር እንደማደርገውና ዛሬ በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ በሰውነቴ ይከብራል ብዬ በድፍረት እናገራለሁ። 21 ስለዚህ ለእኔ ሕይወት ማለት በክርስቶስ መኖር ነው፤ ሞትም ማለት ጥቅም የሚገኝበት ነገር ነው። 22 ይሁን እንጂ በዚሁ ሥጋዊ አካሌ ቀጥዬ የምኖር ብሆን ፍሬ የሚሰጥ ሥራ መሥራት ማለት ነው፤ ሆኖም ግን ቀጥዬ ከመኖርና ከመሞት የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም። 23 በእነዚህ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ተይዤአለሁ፤ በአንድ በኩል ከክርስቶስ ጋር መሆን ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ስለ ሆነ ከዚህ ሕይወት ተለይቼ ከክርስቶስ ጋር መሆንን እፈልጋለሁ ይኸውም ከክርስቶስ ጋር መኖር እጅግ የተሻለ ስለ ሆነ ነው። 24 በሌላ በኩል በሕይወት መኖሬ ለእናንተ የበለጠ አስፈላጊ ነው። 25 በዚህ በመተማመን እኔ ከሞት ተርፌ እምነታችሁ እንዲያድግና ደስታን እንድታገኙ ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ ዐውቃለሁ። 26 እኔም እንደገና ወደ እናንተ ስመጣ በእኔ ምክንያት ያላችሁ ትምክሕት በኢየሱስ ክርስቶስ ይበዛል። 27 እንግዲህ ከሁሉም በላይ ሕይወታችሁ የክርስቶስን ወንጌል የሚያስመሰግን ይሁን፤ ይህም እኔ መጥቼ ባያችሁም ወይም ከእናንተ ብርቅ በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ መቆማችሁንና ወንጌልን በኅብረት ለማዳረስ መጋደላችሁን እሰማለሁ። 28 ተቃዋሚዎቻችሁንም በምንም ነገር አትፍሩአቸው፤ ይህም ድፍረታችሁ ለእነርሱ የመጥፋታቸው ምልክት ሲሆን ለእናንተ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ የመዳኛችሁ ምልክት ነው። 29 ክርስቶስን የማገልገል ዕድል የተሰጣችሁ በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቀበሉም ጭምር ነው። 30 ስለዚህ አሁን ከእኔ ጋር የመከራ ተካፋዮች ሆናችኋል፤ ይህም መከራ ከዚህ በፊት ደርሶብኝ ያያችሁትና አሁንም እየደረሰብኝ መሆኑን የምትሰሙት ነው። |