ናሆም 1:3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ለቁጣ የዘገየ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፤ ጌታ መንገዱ በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ነው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ታጋሽና ኀያል ነው፤ ነገር ግን በደለኛውን ሳይቀጣው አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በሞገድ ውስጥ ነው፤ ሰው ሲራመድ ትቢያን እንደሚያስነሣ፥ የእግዚአብሔርም መገለጥ ደመናን ያስከትላል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ ንጹሕ ነህ አይልም፣ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። |
ለመስማትም እንቢ አሉ፥ በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት አላስታወሱም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፥ ቸር፥ ርኅሩኅ፥ ለቁጣ የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ፥ አልተውካቸውምም።”
ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ጌታ በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።
ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል።
ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፥ ጌታ አምላካችሁም ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።
ወደ ጌታ ጸለየ፥ እንዲህም አለ፦ “ጌታ ሆይ፥ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አስቀድሜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የፈለግሁትም ለዚህ ነበር፥ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ ከክፉ የምትመለስ አምላክ እንደሆንህ አውቄ ነበርና።
ጌታም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ የአምላኩም ቀስት እንደ መብረቅ ይወጣል፤ እግዚአብሔር ጌታም መለከትን ይነፋል፥ ከደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይመጣል።
‘ጌታ ታጋሽና ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ በደልንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን በደል እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው።’
ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።