Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ያዕቆብ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሰላምታ

1 የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ያዕቆብ ለተበተኑ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን።


እምነትና ጥበብ

2 ወንድሞቼ ሆይ! ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ደስታ አድርጋችሁ ቁጠሩት፤

3 ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን እንደሚያጸናችሁ ታውቃላችሁ፥

4 ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን እንድትሆኑ ጽናትም ሥራውን ይፈጽም።

5 ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል።

6 ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ ምክንያቱም የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚነዋወጥ የባሕርን ማዕበል ነው።

7 ያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች አገኛለሁ ብሎ ሊያስብ አይገባውም።

8 በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል ሁለት ሐሳብ ያለው ሰው ነው።


ድህነትና ባለጠግነት

9 ዝቅ ያለው ወንድም ከፍ በማለቱ ይመካ፥

10 ሀብታምም እንደ ሣር አበባ ስለሚረግፍ በውርደቱ ይመካ።

11 የፀሐይ ቃጠሎ በንዳዱ ሲወጣ ሣሩን ያደርቀዋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የመልኩም ውበት ይጠፋል፤ እንዲሁ ሀብታም ሰው በመንገዱ ይዝላል።


ስለ መከራና ፈተና

12 ጌታ ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ተፈትኖ ይቀበላልና፥ በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው።

13 ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ፤” አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱስ ማንንም አይፈትንም።

14 ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው።

15 ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።

16 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! አትታለሉ!

17 መልካም ስጦታ ሁሉ፥ ፍጹምም በረከት ሁሉ፥ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።

18 ለፍጥረቱ የበኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን።


የሰሙትን በሥራ ላይ ማዋል

19 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ይህን አትርሱ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤

20 የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።

21 ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።

22 ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያታለላችሁ፥ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።

23 ቃሉን የሚሰማና የማያደርግ ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤

24 ራሱን አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል።

25 ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል።

26 አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው።

27 በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ፥ “አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች፥ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳት፥ ራስንም ከዓለም ርኲሰት መጠበቅ ነው።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos