ራእይ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)መግቢያና ሰላምታ 1 በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ይህ ነው፤ መልአኩንም ልኮ ራእዩን ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ገለጠ፤ 2 እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት፥ ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱንም ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው። 4 ከዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው፥ ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 5 እንዲሁም ከታመነው ምስክር፥ ከሙታን በኩር ከሆነው፥ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ፤ ለወደደን፥ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ 6 መንግሥትም፥ ለአባቱም ለእግዚአብሔር ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን። 7 እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፤ አሜን። 8 ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ “አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፤” ይላል። የክርስቶስ በራእይ መገለጥ 9 እኔ ዮሐንስ፥ ከእናንተ ጋር አብሬ በኢየሱስ መከራውንና መንግሥቱንና ጽናቱን የምካፈል ወንድማችሁ፥ በእግዚአብሔር ቃልና በኢየሱስ ምስክርነት ምክንያት ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10 በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤ 11 እንዲሁም “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊላደልፊያም ወደ ሎዲቅያም ላክ፤ አለኝ።” 12 የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ፤ 13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14 ራሱና የራሱ ጠጉርም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ 15 እግሮቹም በምድጃ ውስጥ የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውሃዎች ድምፅ ነበረ። 16 በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፤ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚያበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ፤ 18 ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። 19 እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ የሚሆነውን ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።” |