ዘኍል 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሕዝቡ ማመፁ 1 ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፤ በዚያም ሌሊት ሕዝቡ አለቀሰ። 2 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፦ “በግብጽ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! 3 ጌታም በሰይፍ እንድንሞት ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ለምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብጽ መመለስ አይሻለንምን?” 4 እርስ በርሳቸውም፦ “ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ። 5 ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ማኅበር በሆነው ጉባኤ ሁሉ ፊት በግምባራቸው ወድቀው ሰገዱ። 6 ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7 ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም የሆነች ናት። 8 ጌታስ በእኛ ደስ የሚሰኝ ቢሆን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርሷንም ይሰጠናል። 9 ብቻ፥ በጌታ ላይ አታምፁ፤ ለእኛ እንደ እንጀራ ቁራሽ ናቸውና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ ጌታም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው።” 10 ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተማከሩ። የጌታም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ። 11 ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በመካከላቸውም ስላደረግሁት ተአምራት ሁሉ እንኳ እስከ መቼ ድረስ በእኔ አያምኑም? 12 ከርስታቸው እነርሱን ለማጥፋት በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” ሙሴ ለሕዝቡ ማማለዱ 13 ሙሴ ግን ጌታን እንዲህ አለው፦ “ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ 14 ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አቤቱ፥ አንተ በዚህ ሕዝብ መካከል እንደሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15 ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ እንዲህ ይላሉ፦ 16 ‘ጌታ ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ሊያገባቸው አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው።’ 17 አሁንም፥ እባክህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን፤ አንተም እንዲሁ ቃል ኪዳን ያደረግከው እንዲህ ብለህ በተነናገርህ ጊዜ ነው፦ 18 ‘ጌታ ታጋሽና ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ በደልንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን በደል እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው።’ 19 ይህን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልከው፥ እባክህ፥ እንደ ጽኑ ፍቅርህ ብዛት የዚህን ሕዝብ በደል ይቅር በል።” 20 ጌታም እንዲህ አለ፦ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21 ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የጌታ ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22 በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ክብሬንና ተአምራቴን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ እኔን ስለ ተፈታተኑኝ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ፥ 23 በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፥ እነዚህም የናቁኝ ሰዎች ሁሉ አያይዋትም፤ 24 ባርያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለ ተከተለኝ እርሱ ሄዶ ወደ ነበረበት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25 አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው ውስጥ ስለ ተቀመጡ ነገ ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር በኩል በሚወስደው መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።” የመውረር ሙከራው መክሸፉ 26 ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 27 “የሚያጉረመርምብኝን ይህን ክፉ ማኅበር እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጉረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ሰምቻለሁ። 28 እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ 29 በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ ከአጠቃላይም ቁጥራችሁ፥ በእኔ ላይ ያጉረመረሙ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያም በላይ ሆነው የተቈጠሩት ሁሉ፥ 30 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርሷ ላስቀምጣችሁ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31 ነገር ግን ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን ወደ ምድሪቱ አስገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቋታል። 32 እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33 ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት እረኛች ይሆናሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ዝሙታችሁን ይሸከማሉ። 34 ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ እያንዳንዱም ቀን እንደ አንድ ዓመት ሆኖ፥ በደላችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ መከፋቴንም ታውቃላችሁ።’ 35 እኔ ጌታ፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ በእውነት እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።” 36 ምድሪቱንም እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች፥ እነርሱም ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማውራት በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጉረመርሙ ያደረጉ፥ 37 እነዚያ ክፉ ወሬ ስለ ምድሪቱ ያወሩ ሰዎች በጌታ ፊት በመቅሠፍት ሞቱ። 38 ነገር ግን ምድሪቱን ለመሰለል ከሄዱት ከእነዚያ ሰዎች ውስጥ በሕይወት የቀሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ነበሩ። 39 ሙሴም እነዚህን ቃላት ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ። 40 በማግስቱም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ እንዲህ እያሉ ወጡ፦ እነሆ፥ እኛ በዚህ አለን፤ እኛ ኃጢአትን ሠርተናልና ጌታ ወዳለው ስፍራ እንወጣለን። 41 ሙሴም እንዲህ አለ፦ “የጌታን ትእዛዝ ለምን አሁንም ትተላለፋላችሁ? ይህ አይሳካላችሁም። 42 ጌታ በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትሸነፉ አትውጡ። 43 በዚያም አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ ጌታን ከመከተል ተመልሳችኋልና ጌታ ከእናንተ ጋር አይሆንም።” 44 የጌታ ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ ወጥተው ባይጓዙም እንኳ እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ለመውጣት ደፈሩ። 45 በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወረዱ፥ አሸንፈወዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው። |