Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 38 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦

2 “እውቀት በጎደለው ንግግር ምክርን የሚያጨልመው ማነው?

3 እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ታሳውቀኛለህ።

4 ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? ታስተውል እንደሆንህ ተናገር።

5 የምታውቅ እንደሆነ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋም የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?

6-7 አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?

8 ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?

9 ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥

10 ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦

11 እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።

12 በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘህ ታውቃለህን? ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን?

13 የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርሷም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥

14 ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁም እርሱ ይለወጣል፥ ፍጥረትም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል።

15 ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል።

16 ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገበተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?

17 የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን?

18 ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደሆነ ተናገር።

19-20 ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?

21 በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።

22 በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቤተ መዛግብት አይተሃልን?

23 ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለውጊያና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።

24 ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፋፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል?

25-26 ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥

27 ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብ እንዲዘንብ፥ ለፈሳሹ ውኃ መተላለፊያውን፥ ወይም ለሚያንጐደጉድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው?

28 በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይም የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?

29 በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥

30 የቀላዩም ፊት ረግቶአል።

31 በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?

32 ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?

33 የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲፈጸም ማድረግ ትችላለህን?

34 የውኆች ሙላት ይሸፍንህ ዘንድ። ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን?

35 መብረቆች ሄደው፦ ‘እነሆ፥ እዚህ አለን’ ይሉህ ዘንድ፥ ልትልካቸው ትችላለህን?

36 በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?

37-38 የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ደመና ለዝናብ ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?

39-40 በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን?

41 ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos