ኤርምያስ 43:12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን አነድዳለሁ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ያቃጥላቸዋል ይማርካቸዋልም፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም ስፍራ በሰላም ይወጣል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በግብጽ የጣዖትን ቤተ መቅደሶች ያቃጥላል፤ ጣዖቶቹን ይማርካል፤ እረኛ ለምዱን እንደሚደርብ ግብጽን በግዛቱ ላይ ደርቦ ምንም ጒዳት ሳይደርስበት በድል አድራጊነት ይወጣል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በግብፅም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል፤ ያቃጥላቸውማል፤ ይማርካቸውማል፤ እረኛም ልብሱን እንደሚቀምል እንዲሁ የግብፅን ሀገር ይቀምላታል፤ ከዚያም በሰላም ይወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፥ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፥ ከዚያም በሰላም ይወጣል። |
እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር አልፋለሁ፥ በግብጽም ምድር ከሰው እስከ ከብት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።
ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ጌታ በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።
እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ፦ ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።
ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል ጌታ።
ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ።
አክሊልን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማትዋም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች።
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤
በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውጁም፥ ዓላማውንም አንሡ፤ አውጁ፥ ሳትደብቁም እንዲህ በሉ፦ ባቢሎን ተያዘች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ተሰባበረ፤ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ተሰባበሩ።
በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይነጉዱም፥ የባቢሎንም ቅጥር ወድቆአል።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛትዋን ያነሳል፥ ምርኮዋን ይማርካል፥ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶችን አስወግዳለሁ፥ ምስሎችንም ከኖፍ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከግብጽ ምድር ገዢ አይነሳም፥ በግብጽ ምድር ላይ ፍርሃትን አኖራለሁ።
ጌታ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርን አማልክት ሁሉ ያጠፋቸዋልና፤ የሕዝቦችም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች፥ ሁሉም በያሉበት ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንና የተወደዳችሁ ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትሕትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤