Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 30 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ለግብጽ የወጣ ሙሾ

1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አልቅሱ፥ ለቀኑ ወዮ!

3 ቀኑ ቅርብ ነውና፥ የጌታ ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የሕዝቦች ጊዜ ይሆናል።

4 በግብጽ ላይ ሰይፍ ይመጣል፥ የተገደሉት በግብጽ ውስጥ ሲወድቁ፥ በኢትዮጵያ ጭንቀት ይሆናል፤ ብዛትዋን ይወስዳሉ፥ መሠረቶቿንም ያፈርሳሉ።

5 ኢትዮጵያ፥ ፉጥ፥ ሉድ፥ ባዕዳን ሁሉ፥ ኩብና የቃል ኪዳኑ ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።

6 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴቬኔ ድረስ በእርሷ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

7 ባድማ በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።

8 እሳትን በግብጽ ሳነድድ፥ ረዳቶችዋም ሁሉ ሲሰበሩ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

9 በዚያ ቀን ያለ ስጋት የተቀመጠችውን ኢትዮጵያን ለማስፈራራት መልእክተኞች ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ጭንቀት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ መጥቷልና።

10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አጠፋዋለሁ።

11 እርሱና ከሕዝቦች ሁሉ ርህራሄ የሌላቸው ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በሬሳ ይሞላሉ።

12 ወንዞችን አደርቃለሁ፥ ምድሪቱን በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሞላዋን በባዕዳን እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ።

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶችን አስወግዳለሁ፥ ምስሎችንም ከኖፍ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከግብጽ ምድር ገዢ አይነሳም፥ በግብጽ ምድር ላይ ፍርሃትን አኖራለሁ።

14 ጳትሮስን ባድማ አደርጋለሁ፥ በጾዓን እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖ ላይም ፍርድን አመጣለሁ።

15 የግብጽ ምሽግ በሆነችው በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፤ የኖን ብዛት አጠፋለሁ።

16 በግብጽ እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲን ትጨነቃለች፥ ኖ ትሰባበራለች፥ ኖፍ በቀን ጠላቶች ያጠቁአታል።

17 የአቬንና የፊ-ቤሴት ወጣቶች በሰይፍ ይወድቃሉ፥ እነዚህም ተማርከው ይወሰዳሉ።

18 በዚያ የግብጽን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፥ በትሐፍንሔስ ቀኑ ይጨልማል፥ የኃይልዋ ትዕቢት በውስጧ ይጠፋል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ተማርከው ይወሰዳሉ።

19 እንግዲህ በግብጽ ላይ ፍርድን አመጣለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።


በፈርዖን ላይ የተነገረ አዋጅ

20 እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በሰባተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

21 የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ እነሆ እንዲድን በጨርቅ አልተጠቀለለም፥ ሰይፉን ለመያዝ እንዲጠነክር አልታሰረም።

22 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የበረታችውንና የተሰበረችውን ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ እጥለዋለሁ።

23 ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ።

24 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ አኖራለሁ፤ የፈርዖንንም ክንድ እሰብራለሁ፥ እሱም በፊቱ ክፉኛ እንደቆሰለ ሰው ያቃስታል።

25 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፥ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ በአኖርሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

26 ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos