Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 40 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 እግዚአብሔርም ቀጠለ፤ ኢዮብንም እንዲህ አለው፦

2 “በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን የሚችል አምላክን መተቸት ይችላልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።”

3 ኢዮብም መለሰ፤ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦

4 “እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፥ የምመልስልህ ምንድነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።

5 አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፥ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።”

6 ጌታም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦

7 “እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።

8 በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ላይ ትፈርዳለህን?

9 እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጉዳለህን?

10 ግርማንና ልዕልናን ተላበስ እንጂ፥ ሞገስንና ክብርን ተጐናጸፍ።

11 የቁጣህን ሙላት አፍስስ፥ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።

12 ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፥ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።

13 በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፥ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።

14 በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ልታድንህ እንደምትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።

15 አንተን እንደሠራሁ የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፥ እንደ በሬ ሣር ይበላል።

16 እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፥ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።

17 ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፥ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።

18 አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፥ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።

19 እርሱ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ አውራ ነው፥ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።

20 የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል።

21 ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።

22 ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፥ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።

23 እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፥ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።

24 ዐይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?

25 በውኑ አዞውን በመንጠቆ ታወጣለህን? ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?

26 ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር መንጋጋውን ትበሳለህን?

27 በውኑ ወደ አንተ በእጅግ ይማጸናልን? በለሰለሰ ቃል ይናገርሃልን?

28 በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘለዓለም ባርያ ታደርገዋለህን?

29 ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ ለሴት ልጆችህ መዝናኛ እንዲሆን ታስረዋለህን?

30 አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን? ወይስ ነጋዴዎች ያካፋፍሉታልን?

31 በውኑ ቆዳውን በጦር፥ ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?

32 እስቲ እጅህን በላዩ ጫን፥ ፍልሚያውን በሚገባ ታስታውሳለህ፥ ሁለተኛም አይለምድህም።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos