ኢሳይያስ 46 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የባቢሎን ጣዖቶች 1 ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል። 2 ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ፤ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፥ ራሳቸው ግን ተማረኩ። 3 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁን፥ ስሙኝ። 4 እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻችኋለሁ እኔም አነሣችኋለሁ፤ እኔ እሸከማችኋለሁ እኔም አድናችኋለሁ። 5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? 6 ወርቁን ከኮሮጆ የሚያፈስሱ፥ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል። 7 በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል፤ በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፤ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። 8 ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። 9 እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10 በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ “ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ” እላለሁ። 11 ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራለሁ። ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ። 12 እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፤ 13 ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቼአለሁ። |