Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 46 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በግብጽ ላይ የተደረገ ፍርድ

1 ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የጌታ ቃል ይህ ነው።

2 ስለ ግብጽ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት።

3 ጋሻንና አላባሽን አዘጋጁ ወደ ጦርነትም ቅረቡ።

4 ፈረሰኞች ሆይ! ፈረሶችን ለጉሙና ውጡ፥ ራስ ቁርንም ደፍታችሁ በቦታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ።

5 ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል ጌታ።

6 ፈጣኑ መሸሽ አይችልም ኃያሉም አያመልጥም፤ በሰሜን በኩል ባለው በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ እነርሱ ተሰናክለው ወደቁ።

7 እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዞች የሚናወጥ ይህ ማን ነው?

8 ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዞች ይናወጣል፤ እርሱም፦ እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እሸፍናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሏል።

9 ፈረሶች ሆይ! ውጡ፤ ሰረገሎችም ሆይ! ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፉጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ።

10 ያ ቀን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን ነው፤ እርሱም ጠላቶቹን የሚበቀልበት የበቀል ቀን ነው፤ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና።

11 ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ! ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፤ ብዙ መድኃኒቶችን የተጠቀምሺው በከንቱ ነው፤ ለአንቺ መዳኛ የለሽም።

12 ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ውርደትሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።


ባቢሎን ግብጽን እንደምትወጋ

13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደሚመጣና የግብጽን ምድር እንደሚመታ ጌታ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።

14 በግብጽ አውጁ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ እናንተም፦ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና ተነሥ ራስህንም አዘጋጅ በሉ።

15 ኃይለኞችህ ስለምን ተወገዱ? ጌታ ገፍቶአቸዋልና አልቆሙም።

16 እርሱም ብዙዎችን አሰነካከለ፥ እርሱም ደግሞ ወደቀ፤ እርስ በርሳቸውም፦ ተነሡ፥ የአስጨናቂው ሰው ከሆነው ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባትም ምድር እንመለስ ተባባሉ።

17 በዚያም የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን፦ ሰዓቱን የሚያሳልፍ ለፍላፊ ብለው ጠሩት።

18 እኔ ሕያው በመሆኔ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የተባለው ንጉሥ፥ በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል።

19 አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ሴት ልጅ ሆይ! ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠላለችምና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና በምርኮ ስለምትሄጂ ዕቃዎችሽን አሰናጂ።

20 ግብጽ እጅግ የተዋበች ጊደር ናት፤ ነገር ግን የቆላ ዝንብ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል።

21 በእርሷም መካከል ያሉ ቅጥረኛ ወታደሮችዋ እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም።

22 “ጠላቶችዋ በኃይል ዘምተው እንደ እንጨት ቈራጮች በምሳር ይመጡባታልና በደረቱ እንደሚሽሎኮሎክ እባብ ድምፅ ታሰማለች።

23 እነርሱ ስፍር ቊጥር የላቸውምና ከአንበጣም ይልቅ ብዙ ናቸውና የማያሳልፍ ጥቅጥቅ ቢሆንም እንኳ የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል ጌታ።

24 የግብጽ ሴት ልጅ ታፍራለች፤ ለሰሜኑ ሕዝብ ተላልፋ በእጃቸው ትሰጣለች።”

25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤

26 ነፍሳቸውንም በሚሽዋት ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በባርያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ።


ጌታ እስራኤልን ያድናል

27 “ነገር ግን አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁና፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል በደኅንነትም ይቀመጣል፥ እርሱንም ማንም አያስፈራውም።

28 አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል ጌታ፤ አንተንም እንድትሰደድ ያደረግኹባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ እንደጥፋትህ መጠን እቀጣሃለሁ እንጂ ያለ ቅጣት ከቶ አልተውህም።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos