ኤርምያስ 26:13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ታዘዙ። እግዚአብሔርም በእናንተ ላይ ለማምጣት የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የጌታን ድምፅ ስሙ፤ ጌታም በእናንተ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር ይተዋል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አሁንም የአኗኗራችሁንና የሥራችሁን ሁኔታ ለውጣችሁ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይኖርባችኋል፤ ይህን ብታደርጉ በእናንተ ላይ ሊያመጣ ያቀደውን ጥፋት ይመልሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። |
ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና።
ከግብፅ ሀገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ” ያልሁትን ቃሌን ስሙ።
አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፤ ምክርንም እመክርባችኋለሁ፤ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አቅኑ ብለህ ተናገራቸው።”
ስለ እነርሱ የተናገርሁባቸው ሕዝብ ከክፋታቸው ቢመለሱ፥ እኔ አደርግባቸው ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ።
በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተዉምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።”
ምናልባት እያንዳንዳቸው ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።”
ደግሞም፦ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ሥራችሁንም አሳምሩ፤ ታገለግሉአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ ባሪያዎችን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም፤ እኔንም አልሰማችሁኝም።
ምናልባት የይሁዳ ቤት ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ፥ እኔም በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ፥ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል።”
ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ለአንተም ይሻልሃል፤ ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች።
አደርግባችሁ ዘንድ ከአሰብሁት ክፉ ነገር ተመልሻለሁና በዚች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።
እኔ ሕያው ነኝና ኀጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቍርባን የሚሆን በረከትን በኋላ የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ ስለ አገልጋዮቹም ይራራል፤ በያሉበት መሳለቂያ ሆነው እንደ ኖሩ፥ ኀይላቸውም እንደ ደከመ፥ በጠላትም እጅ እንደ ወደቁ አይቶአልና።
እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም በሚዋጉአቸው ሰዎች ፊት ከመከራቸው የተነሣ ይቅር ብሏቸዋልና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው።