ኤርምያስ 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ እንዲጸልይላቸው ሕዝቡ እንደ ጠየቁ 1 የጭፍራ አለቆችም ሁሉ፥ የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ የሐናንያ ልጅ ኢዛንያስ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ መጡ። 2 እንዲህም አሉት፥ “እባክህ ልመናችን በፊትህ ትድረስ፤ ስለ እኛ፥ ስለ እነዚህም ቅሬታዎች ሁሉ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ ዐይኖችህ እንደ አዩን ከብዙ ጥቂት ቀርተናልና። 3 አምላክህ እግዚአብሔርም የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ይንገረን።” 4 ነቢዩ ኤርምያስም አላቸው፥ “ሰምታችኋል፤ እነሆ እንደ ቃላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚመልስልኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ ከእናንተም አንድም ቃል አልሸሽግም።” 5 ኤርምያስንም፥ “አምላክህ እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከህን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን። 6 የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ስለምንሰማ መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን” አሉት። ለኤርምያስ ጸሎት እግዚአብሔር የሰጠው መልስ 7 እንዲህም ሆነ፤ ከዐሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 8 የቃርሔምንም ልጅ ዮሐናንን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፤ 9 እንዲህም አላቸው፥ “ልመናችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 10 አደርግባችሁ ዘንድ ከአሰብሁት ክፉ ነገር ተመልሻለሁና በዚች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። 11 ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ ፊት አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ፥ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 ይቅርታን እሰጣችኋለሁ፤ ይቅርም እላችኋለሁ፤ ወደ ሀገራችሁም እመልሳችኋለሁ። 13 “እናንተ ግን በዚች ምድር አንቀመጥም ብትሉ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ 14 እናንተም፦ አይደለም፤ ሰልፍ ወደማናይባት፥ የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት፥ እንጀራንም ወደማንራብባት ወደ ግብፅ ምድር እንሄዳለን፤ በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥ 15 ስለዚህ እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ! አሁን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ግብፅም ትገቡ ዘንድ በዚያም ትቀመጡ ዘንድ ፊታችሁን ብታቀኑ፤ 16 እናንተ የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብፅ ምድር ያገኛችኋል፤ ስለ እርሱም የምትደነግጡበት ራብ በዚያ በግብፅ ይደርስባችኋል፤ በዚያም ትሞታላችሁ። 17 ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ፥ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን በሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሆንባቸዋል፤ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ያልቃሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይቀርም፤ ማንም አያመልጥም። 18 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ቍጣዬና መቅሠፍቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለጥፋት ለስድብና ለርግማን ትሆናላችሁ፤ ይችንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩአትም። 19 እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ! እግዚአብሔር፦ ወደ ግብፅ አትግቡ ብሎ ተናግሮባችኋልና ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ ዕወቁ። 20 እናንተ፦ ሰለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፤ አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል። 21 እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፤ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም። 22 አሁንም ሄዳችሁ እንድትቀመጡ በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም እንድትሞቱ በእርግጥ ዕወቁ።” |