ኤርምያስ 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል የተናገረውን ቃል የናታን ልጅ ሰፋንያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን የሚወጣ ግን በሕይወት ይኖራል፤ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፤ በሕይወትም ይኖራል። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ይች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በርግጥ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።” 4 አለቆቹም ንጉሡን፥ “ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚያች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ፥ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው ይገደል፤ ለዚህ ሕዝብ ክፋትን እንጂ ሰላምን አይመኝለትምና” አሉት። 5 ንጉሡም ሴዴቅያስ፥ “ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ በእጃችሁ ነው” አለ። 6 ኤርምያስንም ወሰዱት፤ በግዞት ቤትም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓዱም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ። 7 በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። 8 ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ነገረው፥ 9 “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እነዚህ ሰዎች ነቢዩን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በአደረጉት ሁሉ ክፉ አድርገዋል፤ በከተማዪቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።” 10 ንጉሡም ኢትዮጵያዊዉን አቤሜሌክን፥ “ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፤ ነቢዩ ኤርምያስም ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው። 11 አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፤ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፤ ከዚያም ዕላቂ ጨርቅና አሮጌ ገመድ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጕድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደው። 12 ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን፥ “እነዚህን ጨርቆች በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። 13 ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት፤ ከጕድጓድም አወጡት፤ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ። 14 ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን፥ “አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው። 15 ኤርምያስም ንጉሡን ሴዴቅያስን፥ “ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም” አለው። 16 ንጉሡም ሴዴቅያስ፥ “ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፤ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም” ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ። 17 ኤርምያስም ሴዴቅያስን፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች፤ ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም፥ ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18 ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ አንተም ከእጃቸው አታመልጥም” አለው። 19 ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፥ “ወደ ከለዳውያን በኰበለሉ በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል፤ እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው። 20 ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ለአንተም ይሻልሃል፤ ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። 21 ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው። 22 እነሆ በይሁዳ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች፦ ባለሟሎችህ አታልለውሃል፤ አሸንፈውህማል፤ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ። 23 ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።” 24 ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፥ “ይህን ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። 25 አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው፦ ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን፤ አትሸሽገንም፤ እኛም አንገድልህም፤ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ 26 አንተ በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ” በላቸው። 27 አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፤ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተዉ። 28 ኤርምያስም ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤቱ አደባባይ ተቀመጠ። |