ኤርምያስ 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስና ሬካባውያን 1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፤ እንዲህ ሲል፦ 2 “ወደ ሬካባውያን ቤት ሄደህ ተናገራቸው፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አምጥተህ ከክፍሎቹ ወደ አንዲቱ አግባቸው፤ የወይን ጠጅም አጠጣቸው።” 3 የከባስንን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያንና ወንድሞቹንም፥ ልጆቹንም ሁሉ የሬካባውያንን ቤተ ሰብእ ሁሉ ወሰድኋቸው፤ 4 ወደ እግዚአብሔርም ቤት በበረኛው በሰሎም ልጅ በማሴው ጓዳ በላይ ባለው በአለቆቹ ጓዳ አጠገብ ወደ አለው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጎዶልያ ልጅ ወደ ሐናንያ ልጆች ጓዳ አገባኋቸው። 5 በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ፥ “የወይኑን ጠጅ ጠጡ” አልኋቸው። 6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፥ “የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፤ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እናንተና ልጆቻችሁ ለዘለዓለም የወይን ጠጅ አትጠጡ ብሎ አዝዞናልና። 7 በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፤ ዘርንም አትዝሩ፤ ወይንም አትትከሉ፤ አንዳችም አይሁንላችሁ። 8 እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤ 9 የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ፥ ዘርም የለንም። 10 በድንኳን ውስጥ ተቀምጠናል፤ አባታችንም ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ ሰምተናል፤ አድርገናልም። 11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በዚች ምድር ላይ በዘመተ ጊዜ፦ ኑ ከከለዳውያን ሠራዊትና ከሶርያ ሠራዊት ፊት የተነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ፤ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን።” 12 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር። 14 የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃል ተፈጸመ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ ወይን አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ስለ እናንተ ተናገርሁ፤ ሆኖም አልሰማችሁኝም። 15 ደግሞም፦ እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ሥራችሁንም አሳምሩ፤ ታገለግሉአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፤ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ ባሪያዎችን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም፤ እኔንም አልሰማችሁኝም። 16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋል፤ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝም፤ 17 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ።” 18 ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአባታችሁን የኢዮናዳብን ትእዛዝ ሰምታችኋልና፥ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም ሁሉ አድርጋችኋልና፥ 19 ስለዚህ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘለዓለም አይታጣም፥” ይላል የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |