ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰባተኛው ራእይ 1 በሦስተኛውም ቀን በዛፍ ሥር ተቀምጬ ሳለሁ፦ 2 ከዚያች ዛፍ ፊት ለፊት ቃል መጣ፤ “ዕዝራ! ዕዝራ!” ብሎ ጠራኝ፤ እኔም፥ “እነሆኝ ጌታ ሆይ፥” አልሁ፤ ተነሥቼም ቆምሁ፤ 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ለሙሴ ፈጽሜ ታየሁት፤ ወገኖችም ለግብፅ በተገዙ ጊዜ ጳጦስ በሚባል እንጨት ሥር ተናገርሁት። 4 ላክሁትም፤ ወገኖችንም ከግብፅ አወጣኋቸው፤ ሙሴንም ወደ ደብረ ሲና ወሰድሁት፤ ብዙ ቀንም በእኔ ዘንድ አኖርሁት። 5 ብዙ ድንቅን ነገርሁት፤ የዘመናትንም ምሥጢር አሳየሁት፤ ኋለኛውንም ዘመን ነገርሁት። 6 ይህን ነገር ተናገር፤ ይህንም ነገር ሰውር ብዬ አዘዝሁት። 7 አሁንም ለአንተ እልሃለሁ፦ 8 የነገርሁህን ያን ነገር ታውቅ ዘንድ፥ ያየኸው ሕልምህንም፥ የሰማኸውን ትርጓሜውንም በልቡናህ ጠብቀው። 9 ከሰው ለይተው ይወስዱሃልና፥ ከዚህም በኋላ ዓለም እስኪያልፍ ድረስ እንዳንተ ያሉት ባሉበት ቦታ ከልጆች ጋር ትኖራለህ። 10 የዓለም የጐልማሳነቱ ወራት አልፏልና፥ ዘመኑም አርጅትዋልና። 11 ዓለም ለዐሥር ክፍል ተከፍሏልና እስከ ዐሥርም ድረስ ደርሷልና። 12 የዐሥረኛው እኩሌታ ቀርትዋልና። 13 አሁን ግን ቤትህን አዘጋጅ፤ አዘንተኞቻቸውንም ደስ አሰኛቸው፤ ዐዋቆቻቸውንም ልብ አስደርጋቸው፤ እንግዲህ የምታልፍ ሕይወትንም ተዋት። 14 መዋቲ አሳብን እንግዲህ ተወው፤ የሰው ሸክምንም ከላይህ ጣል፤ የሚሞት አሳብንም ተው፤ የማይሞተውንም ልበስ፤ እንግዲህም ወዲህ ከዚህ ዓለም ትሸጋገር ዘንድ አፍጥን። 15 ይች ያየሃት ክፋት ዛሬ ደርሳለችና፤ እንግዲህ ወዲህ ከእርሷ የምትከፋ ዳግመኛ ትደረጋለችና። 16 ዓለም እያረጀና እየደከመ በሚሄድ መጠን እንዲሁ በውስጡ የሚኖሩ ክፋታቸው ትበዛለችና። 17 እውነት ትጠፋለችና፥ አሰትም ትጸናለችና። ይህ ያየኸውም ንስር ይደርስ ዘንድ ይቸኵላልና።” 18 እኔም መለስሁለት፤ እንዲህም አልሁት፥ “እንግዲህስ ወዲህ በፊትህ እናገራለሁ። 19 አቤቱ፥ እኔ እሄዳለሁና፥ እንደ አዘዝኸኝም ዛሬ ያሉትን ሕዝብ አስተምራቸዋለሁና። እንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ የሚወለዱትን ማን ያስተምራቸዋል? 20 ዓለም በጨለማ ውስጥ አለና፤ በውስጡ ለሚኖሩትም ብርሃን የላቸውም። 21 ኦሪትህ ተቃጥላለችና፥ የሠራኸውን፥ ትሠራውም ዘንድ ያለህን የሚያውቀው የለምና። 22 በፊትህስ ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ ቅዱስ መንፈስህን ላክልኝ፤ እኔም ሰው የሕይወት መንገድን ማግኘት ይችል ዘንድ፥ ሊኖሩ የሚወድዱ ሰዎችም ይድኑ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በዓለም የሆነውን ሁሉና በኦሪትህ ውስጥ ተጽፎ ያለውን እጽፋለሁ።” 23 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ሄደህ ወገኖችህን ሰብስባቸው፤ እስከ አርባ ቀንም ድረስ እንዳይፈልጉህ ንገራቸው። 24 አንተ ግን ብዙ ብራና አዘጋጅ፥ ከአንተም ጋራ ሶርያን፥ ደርብያን፥ ሰላምያን፥ ኢቀናንንና አሳሄልን እኒህን አምስቱን ሰዎች ውሰዳቸው። እነርሱ በመጻፍ ጠቢባን ናቸውና። 25 ወደዚህ ና፤ በልቡናህም የጥበብ መብራትን አበራለሁ፤ ትጽፍም ዘንድ ያለህን ሁሉ እስክትጨርስ ድረስ እንግዲህ አትጠፋም። 26 በጨረስህ ጊዜ ግልጥ የምታደርገው አለ፤ የምትሠውረውም አለ፤ ለዐዋቂዎችም፥ ለጠቢባንም ትሰጣቸዋለህ፤ ነገ በዚህ ሰዓት ትጽፍ ዘንድ ትጀምራለህ።” 27 እንደ አዘዘኝም ሄጄ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰብሁ። 28 እንዲህም አልኋቸው፥ “እስራኤል፥ ይህን ነገር ስሙ። 29 አባቶቻችሁ ቀድሞ በግብጽ ምድር ኖሩ፤ ከዚያም ተቤዣቸው። 30 የሕይወት ሕግንም ተቀበሉ፤ ግን አልጠበቁም፤ ከእነርሱም በኋላ ያላችሁት እናንተ ካዳችሁት። 31 ምድረ ርስትን ሰጠን፤ የጽዮንንም ምድር አወረሰን፤ እናንተም፥ አባቶቻችሁም ካዳችሁት፤ እርሱንም መበደል አልተዋችሁም፤ የአዘዛችሁ የልዑል መንገድን አልጠበቃችሁም። 32 እርሱ እውነት ፈራጅ ነውና በጊዜው የሰጣችሁን ቀማችሁ። 33 አሁንም እናንተ በዚህ አላችሁ፤ ወንድሞቻችሁ ግን ከእናንተ ተለይተው በውስጥ ናቸው። 34 ልቡናችሁን ያስገዛችሁት፥ ሕሊናችሁንም የገሠጻችሁት እንደ ሆነ፥ ሕይወታችሁንም የጠበቃችሁት እንደ ሆነ አትሞቱም። 35 ከሞት በኋላ ፍርድ ይመጣልና፥ እኛንም በሕይወት አያኖረንምና፥ ያንጊዜም የጻድቃን ስማቸው ይገለጣል፤ የኃጥኣንም ሥራቸው ይገለጣል። 36 ከእናንተ ወደ እኔ የሚመጣ አይኑር፤ እስከ አርባ ቀንም ድረስ አትፈልጉኝ።” 37 እንዳዘዘኝም እነዚያን አምስቱን ሰዎች ይዤ ወደ ምድረ በዳው ሄድን፤ በዚያም ተቀመጥን። 38 በማግሥቱም ቃል መጣ፥ “ዕዝራ! ዕዝራ!” ብሎ ጠርቶ እንዲህ አለኝ፥ “አፍህን ክፈት እኔም የማጠጣህን ጠጣ።” 39 አፌንም በከፈትሁ ጊዜ ውኃ የተመላ፥ መልኩ እሳት የሚመስል መጠጥን አጠጣኝ። 40 ተቀብዬም ጠጣሁት፤ ልቡናዬም ፈጽሞ ዕውቀትን ተናገረ፤ ዕውቀትም በልቡናዬ በዛ፤ ነፍሴም ትጠብቀዋለች፤ ታስበዋለችም። 41 አፌም ተከፈተ፤ ከዚያም ወዲያ ዝም አላለም። 42 ልዑልም ለእነዚያ ለአምስቱ ሰዎች ጥበብን ሰጣቸው፤ የማያውቁትንም ምልክት የሆነውን ይህን ሁሉ በማከታተል ጻፉ፤ በዚያም አርባ ቀን ተቀመጡ፤ እነርሱም ቀን ቀን ይጽፉ ነበር፤ ማታ ማታም እህል ይመገቡ ነበር፤ 43 እኔ ግን ቀን እናገራለሁ፤ ሌሊትም ዝም አልልም። 44 በእነዚያ በአርባ ቀኖችም ሃያ አራት መጻሕፍት ተጻፉ። 45 ከዚህም በኋላ እነዚያ አርባ ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ልዑል ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “አስቀድሞ የጻፋችሁትን ያን ግልጥ አድርገው፤ የሚገባውም የማይገባውም ሁሉ ያንብበው። 46 ይህን ግን ለጠቢባን ሕዝብ ትሰጣቸው ዘንድ ጠብቅ። 47 በእነዚህ ውስጥ የማስተዋል መብራት፥ የጥበብ ምንጭ፥ የዕውቀትም ፈሳሽ አለና።” 48 እንዲሁም አደረግሁ፤ በአራተኛው ዓመት፥ ከዓመታቱ ሱባዔያት በአምስተኛው ሱባዔ፥ ከፍጥረተ ዓለም በኋላ በአምስት ሺህ ዓመታት፥ ጨረቃ ሠርቅ ባደረገች በዐሥረኛው ቀን በሦስተኛው ወር፥ በዘጠና አንድ ቀናት። 49 ያንጊዜ ይህን ሁሉ ከጻፈ በኋላ ዕዝራን ይዘው እንደ እርሱ ያሉ ሰዎች ወዳሉበት ሀገር ወሰዱት፤ እርሱም እስከ ዘለዓለም ድረስ የልዑል የጥበቡ ጸሓፊ ተባለ። የዕዝራ መጽሐፍ ተፈጸመ፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባው፤ ለዘለዓለሙ አሜን። |