ሙሴ1 ሙሴም ስም አጠራሩ የተባረከ ነው፤ መታሰቢያውና አምሳሉም እንደ ቅዱሳን ክብር ነው። 2 ከፍ ከፍም አደረገው፤ በጠላቶቹም ላይ የሚያስፈራ ሆነ። 3 በቃሉም ተአምራትን አደረገ፤ በነገሥታቱም ፊት አከበረው፤ ስለ ሕዝቡም አዘዘው፤ ክብሩንም አሳየው። 4 ስለ ሃይማኖቱና ስለ የዋህነቱም ቀደሰው፤ ከሰውም ሁሉ እርሱን መረጠው። 5 ቃሉንም አሰማው፤ ወደ ደመናውም ውስጥ አገባው፤ ትእዛዙንም በፊቱ ሰጠው፤ ለያዕቆብ ቃል ኪዳኑን፥ ለእስራኤልም ፍርዱን ያስተምር ዘንድ የሕይወት ሕግን ሰጠው። አሮን6 ከሌዊ ወገን የተወለደ ወንድሙ አሮንም እንደ እርሱ ታላቅ ነው፤ ቅዱስም፥ የከበረም ነው። 7 የዘለዓለም ሕግንም አጸናለት፤ በሕዝቡም መካከል ክህነትን ሰጠው፤ በአማረ ጌጥም አስደነቀው፤ የክብር ልብስንም አለበሰው። 8 በሁሉም ዘንድ አስመካው፤ በከበሩ ልብሶችም አጸናው፤ እጀ ሰፊና እጀ ጠባብንም፥ ኤፉድንም አለበሰው። 9 በዙሪያውም ብዙ ሮማንና የወርቅ ጸናጽል አለ፤ በእግሩም በረገጠ ጊዜ የመርገፉ ድምፅ በቤተ መቅደስ ይሰማ ዘንድ ይጮህ ነበር፤ ይህም ለሕዝቡና ለልጆቻቸው መታሰቢያ ሆነ። 10 የተለየ ሰማያዊ ሐር ያለበት አራት ኅብርን፥ አምስተኛ ወርቀ ዘቦ ያለበት በነጭ ሐር የተሠራ ልብስንም፥ በሚገባና በእውነት ነገር የተሠራ ልብሰ መትከፍ አለበሰው። 11 የነጭ ሐር የሚሆን ፈትሉ እጥፍ የሆነ፥ ዕንቍም ያለበት፥ የማኅተምም ቅርጽ ያለበት ልብስን በልብስ ላይ አለበሰው፤ እጀ ጠባቡም በወርቅ የተሠራ ነው፤ በየወገናቸው መታሰቢያ ሊሆን በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልጆች ቍጥር ልክ የተጻፈ ነው። 12 በማኅተም መልክ አምሳል የተሠራ የወርቅ አክሊልን በዝግራ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት፤ የተለየ የክብሩ መመኪያ የሚሆን ተአምራት የሚያደርግበት፥ ለዐይን የተወደደ፥ ጌጡ ፈጽሞ ያማረ የወርቅ መጠምጠሚያን በዝግራ መጠምጠሚያው ላይ አደረገለት። 13 ከእርሱ አስቀድሞ እንደ እርሱ ልብስ ያለ ልብስ አልተሠራም፤ ከልጆቹ ብቻ በቀር፥ ለዘለዓለም ከዘመዶቹም በቀር እንደ እርሱ የለበሰ የለም። 14 ሁልጊዜ በየዕለቱ የጧትና የማታ መሥዋዕት ይሠዉለት ዘንድ፥ 15 ሙሴም እጃቸውን ቀባላቸው፤ የተቀደሰውንም ዘይት ቀባው፤ ለዘለዓለሙም ሕግ ሆነው፤ ይገዙለት ዘንድ፤ ካህናትም ይሆኑት ዘንድ፤ ሕዝቡንም በስሙ ይባርኳቸው ዘንድ፤ ሰማይ ጸንቶ በሚኖርበት ዘመን ልክ ለልጆቹ ሕግ ሆናቸው። 16 ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ፥ የበጎ መዓዛ መታሰቢያም ሊሆን ዕጣንን ያጥን ዘንድ፥ ለሕዝቡም ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸው ዘንድ ከሕያዋን ሁሉ እርሱን መረጠ። 17 ትእዛዛቱን ሰጠው፤ ለያዕቆብ ምስክሩን ያስተምረው፥ ለእስራኤልም ሕጉን ያስተምረው ዘንድ ፍርድንና ሥልጣንን ሰጠው። 18 ሌሎች ግን ተቃወሙት፤ የዳታንና የአቤሮን የሆኑ ሰዎች፥ የእነቆሬም ሠራዊት በመናደድና በመቈጣት በምድረ በዳ ቀኑበት። 19 እግዚአብሔርም አያቸው፤ ደስም አላሰኙትም፤ ተቈጥቶም አጠፋቸው፤ በእነርሱም ላይ ድንቅ ተአምራትን አደረገ፤ በእሳትም አጠፋቸው። 20 ለአሮንም ክብርን ጨመረለት፤ የእህላቸውንም ቀዳምያት ዕድል ፋንታ አድርጎ ሰጠው። 21 ለእርሱና ለልጆቹም የሰጣቸውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ይበሉ ዘንድ፥ የሚያጠግባቸው ዐሥራቱን አስቀድሞ ሠራላቸው። 22 የሕዝቡንም ምድር አልተካፈለም፤ ከሕዝቡም ጋራ ርስትን አልወረሰም፤ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ዕድሉ፥ ርስቱም ነውና። ፊንሐስ23 የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በክብር ሦስተኛ ነው፤ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶአልና፥ ሕዝቡንም ለማስተማር አስነሥቶታልና፥ በልቡናው ቸርነትም ከእግዚአብሔር ፈቃድ የተነሣ ለእስራኤል አስተሰረየ። 24 ስለዚህም ለሕዝቡ የቅዱሳንን ሥርዐት ያስተምራቸው ዘንድ፥ ለእርሱና ለዘሩም ለዘለዓለም ደገኛ ክህነት ይሆን ዘንድ የሰላም ኪዳንን አጸናለት። 25 ከነገደ ይሁዳ ለተወለደ ለዳዊት ልጅም ጌጥ ይሆን ዘንድ፥ በሕጉ ጸንቶ የሚኖር የልጁ መንግሥትም እድል ይሆን ዘንድ፤ 26 በልቡናቸውም ጥበብን ያሳድርባቸው ዘንድ፥ በዘመናቸው ሁሉ ክብራቸውና በረከታቸው እንዳይጠፋባቸው፥ ወገኖቹንም በእውነት ይገዟቸው ዘንድ ከልጆቹ ጋራ ለእርሱ ክህነት ርስቱ ነው። |