ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 46 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢያሱና ካሌብ 1 የነዌ ልጅ ኢያሱም በሰልፍ ውስጥ ጽኑዕ ነው። ከሙሴም ቀጥሎ ትንቢት ተናገረ፤ እንደ ስሙም ታላቅ ሆነ፤ እግዚአብሔር የመረጣቸውንም ከመከራ አዳናቸው፤ ለእስራኤል ምድራቸውን ያወርሳቸው ዘንድ ጠላቶቻቸውን ተበቅሎ አጠፋ። 2 እጁን በአነሣ ጊዜ፥ በከተሞቻቸውም ላይ ጦሩን በወረወረ ጊዜ ከበረ። 3 ከእርሱ አስቀድሞ እንደ እርሱ የሆነ ማንነው? እርሱ እግዚአብሔርም ጠላቶቹን ተዋጋለት። 4 ፀሐይ በቃሉ የቆመች አይደለምን? አንዲቱስ ቀን ሁለት ቀን የሆነች አይደለምን? 5 በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹ በአስጨነቁት ጊዜ ኀያልና ልዑል እግዚአብሔርን ጠራው፤ ገናና እግዚአብሔርም በበረድና በጽኑዕ ኀይል መለሰለት። 6 በተጣሏቸው በአሕዛብም ላይ አዘነበባቸው፤ የተዋጓቸውንም በገደል ውስጥ አጠፏቸው፤ ሕዝቡ ኀይሉን ያውቁ ዘንድ የሚዋጋላቸው እግዚአብሔር ነውና፤ ኀይሉን አከታትሎ ከእነርሱ ጋር አደረገላቸው። 7 በሙሴም ዘመን ከእነርሱ ጋር ይቅርታን አደረገ፤ እርሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በጠላት ፊት ተከራከሩ፤ ሕዝቡንም በደልን ከለከሏቸው፥ ክፉ እንጕርጕሮንም አስተዉአቸው። 8 ከስድስት መቶ ሺህ አርበኞችም የዳኑ እነርሱ ሁለቱ ብቻ ናቸው፤ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ወደ ከነዓንም ገቡ። 9 እግዚአብሔርም ለካሌብ ኀይልን ሰጠው፤ እስኪያረጅም ድረስ ከእርሱ ጋራ ኖረ፤ ወደ ከፍተኛውም ምድር አወጣው። ልጆቹም ርስታቸውን ተካፈሉ። 10 የእስራኤል ልጆች ሁሉ እግዚአብሔርን መከተል መልካም እንደ ሆነ ያውቁ ዘንድ። መሳፍንት 11 በየስማቸው የተጠሩ የእስራኤል መሳፍንት፥ ልቡናቸውም ያልሰሰነ ሰዎች ሁሉ፥ እግዚአብሔርንም ያልተዉት ሰዎች ሁሉ፥ ስም አጠራራቸው የተባረከ ይሁን። 12 በኖሩበትም ሀገር አጥንቶቻቸውን ደስ ይበላቸው፤ ልጆቻቸውም ይባረኩ፥ ይክበሩ። 13 ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ዘንድ ነቢይ ነበር፤ ለሕዝቡ ንጉሥን ቀብቶ አነገሠ። 14 በእግዚአብሔርም ሕግ ማኅበሩን ገዛ፤ እግዚአብሔርም ያዕቆብን አከበረው። 15 በእምነቱም ትንቢት ጸና፤ በቃሉም እውነተኛ ራእይ ተገለጠ። 16 የበግም ጠቦት ሲሠዋ ጠላቶቹ ከብበው በአስጨነቁት ጊዜ ኀያል እግዚአብሔርን ጠራው። 17 እግዚአብሔርም በሰማይ አንጐደጐደ፤ በታላቅ ጩኸትም ድምፁን አሰማ። 18 የፍልስጥኤምንና የጤሮስንም ነገሥታት ሁሉ አጠፋቸው። 19 የሚሞትበትም ቀን ሳይደርስ ለእግዚአብሔርና ለመሢሑ፥ የማንንም ሰው ገንዘብ ከገንዘባቸው እስከ ጫማ ድረስ እንዳልወሰደ፥ ከእነርሱም የከሰሰው እንደሌለ አዳኘ። 20 ከሞተም በኋላ ትንቢት ተናገረ፤ የንጉሡንም ሞት ተናገረ፤ ከምድርም ተነሥቶ ቃሉን በትንቢት ከፍ አደረገ። የሕዝቡንም በደል አጠፋ። |