የጦቢት ልጅ ጉዞ ዓሣው1 እርሷም ማልቀስዋን ተወች። 2 ልጁም ከመልአኩ ጋር ሄደ፥ ውሻውም ከኋላ ተከትሎአቸው ሄደ፥ ሲሄዱ ዋሉና ሲመሽ በጢግሮስ ወንዝ አጠገብ አረፉ። 3 ልጁ እግሩን ሊታጠብ ወደ ወንዝ ወረደ፥ አንድ ትልቅ ዓሣም ከውሃው ውስጥ ዘሎ በመውጣት እግሩን ሊውጠው ተወረወረ፤ ልጁም ጮኸ። 4 መልአኩም “ዓሣውን ያዘው አትልቀቀው” አለው። ልጁም ዓሣውን ይዞ እየጐተተ ወደ ባህሩ ዳር አወጣው። 5 መልአኩም “ዓሣውን እረደውና ሐሞቱን፥ ልቡንና ጉበቱን አውጣው፤ እነዚህን ያዝና የሆድ እቃውን ወዲያ ጣለው፤ ሐሞቱ፥ ልቡና ጉበቱ ለመድኃኒትነት ይጠቅማልና” አለው። 6 ልጁ ዓሣውን ቀዶ ከፈተውና ሐሞቱን፥ ልቡንና ጉበቱን ወሰደ፥ ከዚህ በኋላ ዓሣውን ጠበሰና በሉት፤ የቀረውን ለጉዞ በጨው ቀመመው፤ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ወደ ሜዶንም ተቃረቡ። 7 ከዚህ በኋላ ልጁ መልአኩን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ወንድሜ አዛርያ የዓሣው ልብ ጉበትና ሐሞት ምን ለመፈወስ ይጠቅማል?” 8 እሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የዓሣውን ልብና ጉበት ጋኔን ወይም ክፉ መንፈሰ በያዘው ወንድ ወይም ሴት ፊት ካጨስከው በሽታው ይለቃቸዋል፥ አይመለስባቸውምም። 9 ሐሞቱ ግን ዐይኖቹ ላይ ብልዝ ለጣለበት ሰው በቅባትነት ያገለግላል፥ ከተጠቀምክ በኋላ እፍ ብትለው ብልዞቹ ይጠፋሉ።” 10 ወደ ሜዶን ደረሱ፥ ወደ አቅባጥናም ተቃረቡ። 11 ሩፋኤል ልጁን “ወንድሜ ጦብያ” አለው። እርሱም “አቤት” አለው። መልአኩም ቀጠለና “ዛሬ ሌሊት ማደር የሚገባን በዘመድህ በራጉኤል ቤት ነው፥ ሣራ የምትባል ልጅ አለችው፤ 12 ከሣራ በቀር ሌላ ልጅ የለውም፥ የእርሷ የቅርብ ዘመድዋ አንተ ነህ፥ እርሷን ለማግባትና የአባትዋን ሀብት ለመውረስ ከማንም በላይ መብት ያለህ አንተ ነህ፤ እርሷም አዋቂ፥ ብርቱና መልከ መልካም ናት፥ አባትዋም በጣም ይወዳታል 13 አንተ እርሷን ለማግባት መብት አለህ፥ ስማኝ ወንድሜ፥ ይህች ልጃገረድ ያንተ እጮኛ እንድትሆን ዛሬውኑ ለአባትዋ እኔ እናገራለሁ፥ ከራጌስ ስንመለስ ሰርጉን እንደግሳለን፥ ራጉኤል አንተን ከልክሎ ለሌላ ሊድራት እንደማይችል አረጋግጥልሃልሁ፥ ምክንያቱም ልጅቷን ላንተ መዳር እንደሚገባው እያወቀ ለሌላ ሰው ቢድራት በሙሴ መጽሐፍ መሠረት በሞት ይቀጣል። ስለዚህ ወንድሜ ምክሬን ስማ፥ ዛሬ ማታ ስለ ልጅቷ ተነጋግረን ለጋብቻ እንጠይቃታለን፥ ከራጌስ ስንመለስ ከእኛ ጋር ወደ ቤት ይዘናት እንሄዳለን።” 14 ጦብያ ለሩፋኤል እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ወንድሜ አዛርያ እስዋ ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ባል እንዳገባችና ሰባቱም ባሎችዋ በሰርጉ ቀን ወዳለችበት ጫጉላ ሲገቡ እንደሞቱ ሰምቻለሁ። ወደ እርሷ በገቡበት በዚያች ሌሊት ይሞታሉ። የገደላቸውም አንድ ጋኔን መሆኑን ሰምቻለሁ። 15 እኔም ፈርቻለሁ፤ ጋኔኑ ስለሚወዳት እርሷን አይጐዳትም፥ ወደ እርሷ መቅረብ የሚፈልገውን ሰው ግን ወዲያውኑ ይገድለዋል። እኔም ለአባቴ አንድ ልጅ ነኝ መሞትም አልፈልግም፥ አባትና እናቴ በቀሪው ዘመናቸው ሁሉ በእኔ እያዘኑ እንዲኖሩ አልፈልግም። የሚቀብራቸውም ሌላ ልጅ የላቸውም።” 16 መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ከአባትህ ወገን የሆነች ሴት እንድታገባ ብሎ አባትህ የመከረህን ረሳኸው? ስማኝ ወንድሜ! ስለ ጋኔኑ እንደሆነ አትጨነቅ፥ አግባት፤ ዛሬ ማታ ሚስት እንድትሆንህ እንደሚሰጡህ አውቃለሁ። 17 ስለዚህ ወደ ጫጉላው ቤት ከገባህ በኋላ፥ ከዓሣው ጉበትና ልብ ጥቂት ወስደህ በዕጣን ማጨሻ ላይ አድርገው፤ 18 ጋኔኑ ጭሱ ሲሸተው ሽሽቶ ይሄዳል ወደ እርሷም ከቶ ተመልሶ አይመጣም። አብራችሁ ከመተኛታችሁ በፊት ሁለታችሁም ለመጸለይ ተነሱ፥ የሰማዩ ጌታ ጸጋውንና ከለላውን እንዲሰጣችሁ ለምኑት። አትፍራ! ከጥንት ጀምሮ እርሷ የተወሰነችው ለአንተ ነው፥ የምታድናትም አንተ ነህ። ቃሌን እሰጥሃለሁ እርሷ አንተን ትከተላለች፥ እንደ ወንድሞች የሚሆኑልህ ልጆችንም ትወልድልሃለች፥ አትጨነቅ።” ጦቢያ የሩፋኤልን ንግግር ባደመጠ ጊዜና እርሷ ከዘሩና ከአባቱ ወገን የሆነች እኀቱ መሆንዋን ባወቀ ጊዜ በጣም ወደዳት፥ ልቡም ከእርሷ ጋር ሆነ። |