Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽ​ሐፈ ጦቢት 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ወደ ኤቅባጥና ከተማ በገቡ ጊዜ ጦብያ “ወንድሜ አዛርያ በቀጥታ ወደ ወንድማችን ወደ ራጉኤል ቤት ውሰደኝ” አለው። እሱም ወደ ራጉኤል ቤት ወስደው፤ ራጉኤልም በግቢው አጥር በር አጠገብ ተቀምጦ አገኙት፤ እነርሱ አስቀድመው ሰላምታ አቀረቡለት። እርሱም “እንደምናችሁ ወንድሞቼ፥ እንኳን ደኀና መጣችሁ” አለና ወደ ቤቱ አስገባቸው።

2 ሚስቱ ኤድናን “ይህ ወጣት ወንድሜ ጦቢትን እንዴት ይመስላል!” አላት።

3 ኤድናም “ወንድሞቼ ከየት ነው የመጣችሁት?” አለቻቸው። እነርሱም “ወደ ነነዌ ከተሰደዱት ከኒፍታሊ ልጆች መካከል ነን” አሏት።

4 እርሷም “ወንድማችን ጦቢትን ታውቁታላችሁን?” አለቻቸው። እነርሱም “አዎን እናውቀዋለን” አሏት። እርሷም “እንዴት ነው?” አለቻቸው።

5 እነርሱም “በሕይወት አለ፤ ደኀና ነው” አሏት። ጦብያም ቀጠል አድርጎ “አባቴ ነው” አለ።

6 በዚያን ጊዜ ራጉኤል ብድግ አለና ሳመው፥ አለቀስም።

7 ቀጥሎም “ተባረክ ልጄ! የደግ አባት ልጅ ነህ። እንዲህ ያለ ብሩህና መልካም የሚሠራ ሰው ዐይኖቹን ማጣቱ እንዴት ያሳዝናል” አለ። በዘመዱ ጦቢያ አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ።

8 ሚስቱ ኤድናም ስለ እርሱ አለቀሰች፥ ልጃቸው ሣራም አለቀሰች።

9 ከዚህ በኋላ ራጉኤል አንድ የበግ ሙክት አርዶ መልካም መስተንግዶ አደረገላቸው። ታጠቡና ለመብላት በማዕድ ተቀመጡ፥ ጦብያ ሩፋኤልን “ወንድሜ አዛርያ ዘመዴ የሆነችውን ሣራን እንዳገባ ራጉኤልን ጠይቀው” አለው።

10 ራጉኤል ንግግሩን ሰምቶ ወጣቱን እንዲህ አለው፦ “ብላ፥ ጠጣ ዛሬ ማታ ተደሰት፤ ወንድሜ ሆይ ልጄ ሣራን ካንተ በቀር ሌላ ሊያገበት መብት የለውም፤ እኔ እንኳን ልሰጣተ ብፈልግ አንተ የቅርብ ዘመዷ ስልሆንህ ላንተ እንጂ ለሌላ ልሰጣት አልችልም። ነገር ግን ልጄ ሆይ እውነቱን ልንገርህ፥

11 ከዚህ ቀደም ከወገኖቻችን መካከል ከሰባት ሰዎች ጋር አጋብቻት ነበር፤ ሁሉም በመጀመሪያው ቀን ማታ ወደ ክፍሏ ሲገቡ ሞቱ። ለአሁን ግን ልጄ ብላ፥ ጠጣ፥ ጌታ ጸጋውንና ሰላሙን ይሰጥሃል።” ጦብያም “የእኔን ነገር እስክትወስንልኝ ምንም አልበላም፥ አልጠጣም” አለ። ራጉኤልም እንዲህ አለው “መልካም፤ በሙሴ መጽሐፍ መሠረት ለአንተ ተሰጥታለች፥ ለአንተ እንድትሰጥ ሰማይ እራሱ ደንግጓል፥ ስለዚህ እኀትህን ለአንተ ሰጥቻታለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ ወንድሟ ነህ፥ እርሷም እኀትህ ናት። ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም ለአንተ ተሰጥለች። ልጄ የሰማዩ ጌታ በዚህች ሌሊት ሞገስ ይሁናችሁ፤ ጸጋውንና ሰላሙን ይስጣችሁ።”

12 ከዚህ በኋላ ራጉኤል ልጁን ሣራን ጠራትና መጣች፤ በእጇም ያዛትና ለጦብያ እንዲህ በማለት ሰጠው “ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ሕጉና በሙሴ መጽሐፍ የተጻፈው ውሳኔ ሚስት አድርጎ ሰጥቶሃል፤ ውሰዳት፥ ወደ አባትህም ቤት በደኅና አድርሳት፤ የሰማይ አምላክ በሰላም ያድርሳችሁ።”

13 ቀጥሎም እናቷን ጠራና የሚጽፍበትን ወረቀት እንድትሰጠው ጠየቃት። የሙሴ መጽሐፍ በደነገገው መሠረት ሚስቱ እንድትሆን የጋብቻውን ውል ጽፎ ሰጠው።

14 ከዚህ በኋላ መብላትና መጠጣት ጀመሩ።

15 ራጉኤል ሚስቱን ኤድናን ጠራና “እኀቴ ሁለተኛውን ክፍል አዘጋጂና እርሷን ወደዚያ ውሰጀት” አላት።

16 እርሷም እንዳላት ሄዳ በዚሁ ክፍል አልጋውን አዘጋጀች። ልጅቷንም ወደዛ ወሰደቻት፤ ማልቀስም ጀመረች፥ ዕንባዋንም ጠረገችና፦

17 “በርቺ ልጄ፥ የሰማዩ ጌታ ኀዘንሽን ወደ ደስታ ይለውጠው፥ አይዞሽ ልጄ” ብላት ወጣች።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች