ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሩፋኤል 1 ከዚህ በኋላ ጦብያ ለአባቱ ለጦቢት እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አባቴ ያዘዝኸኝን ሁሉ እፈጽማለሁ። 2 ግን ሰውዬው አያውቀኝም እኔም አላውቀውም ይህን ገንዘብ ከእሱ እንዴት ማግኘት እችላለሁ? እንዲያውቀኝና እንዲያምነኝ ገንዘቡንም እንዲሰጠኝ ምን ምልክት እሰጠዋለሁ? ወደ ሜዶን የሚወስደውንም መንገድ አላውቀውም።” 3 ጦቢት ለልጁ ለጦብያ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንድ ወረቀት ፈርመልኝ፤ እኔም እዚያው ላይ ፈርሜአለሁ የተፈረመውን ወረቀት በሁለት ገምሼ ከገንዘቡ ጋር አድርጌዋለሁ። ይህን ገንዘብ ከሰውዬው ዘንድ ካስቀመጥሁ አሁን ሃያ ዓመት ሆኖአል። እንግዲህ ልጄ ሆይ የሚከተልህ አንድ የታመነ የመንገድ ጓደኛ ፈልግ፤ ወስዶ ሲመልስህ ደሞዙን እንከፍለዋለን፤ ሂድና ገንዘብ ከገባኤል ተቀበል።” ጦቢት 4 ጦቢያ ወደ ሜዶን መንገዱን የሚያውቅና ከእርሱም ጋር የሚሄድ ሰው ለመፈለግ ወጣ። ጦብያ ሲወጣ ከፊት ለፊቱ መልአኩ ሩፋኤል ቆሞ አገኘው፤ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ግን አላወቀም። 5 “ከወዴት ነህ ወንድሜ?” አለው። እርሱም “እኔ ከወገኖችህ የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ፤ እዚህ የመጣሁት ለመሥራት ነው” አለው። ጦብያም “ወደ ሜዶን የሚወስደውን መንገድ ታውቀዋለህን?” አለው። 6 ሌላኛውም “አዎን አውቀዋለሁ፥ ብዙ ጊዜ ወደዚያ ተመላልሻለሁ፤ መንገዶቹን ሁሉ ደኀና አድርጌ አውቃቸዋለሁ፥ ብዙ ጊዜ ወደ ሜዶን ሄጃለሁ፥ የማርፈውም በሜዶን አገር በራጌስ በሚኖረው ወንድማችን በሆነው በገባኤል ቤት ነው፤ ከኤቅባጥና ወደ ራጌስ ሁለት ቀን ያስኬዳል፥ ምክንያቱም ራጌስ የምትገኘው በተራራው ላይ ሲሆን ኤቅባጥና ደግሞ በሜዳው መሃል ነው።” 7 ጦብያ “አባቴን ነግሬው እስክመጣ ቆየኝ ወንድሜ፤ አንተ ከእኔ ጋር እንድትመጣ እፈልጋለሁ፥ ደሞዝህንም እከፍልሃለሁ” አለው። 8 እርሱም “መልካም፥ እጠብቅሃለሁ፤ ግን እንዳትቆይ” አለው። 9 ጦብያም ለአባቱ ለመንገር ወደ ቤት ገባና “እነሆ ከወንደሞቻችን ከእስራኤላውያን አንድ ሰው አግኝቻለሁ” አለው። ጦቢትም “ከየትኛው ቤተሰብና ነገድ መሆኑን ለማወቅና የመንገድ ጓደኛህ ለመሆን እምነት የሚጣልበት መሆኑን ለመገንዘብ እስቲ ሰውዬውን ጥራልኝ ልጄ ሆይ” አለው። ጦብያም ሊጠራው ወጣና “ወንድሜ አባቴ ሊያይህ ይፈልጋል” አለው። 10 መልአኩ ወደ ቤት ገባ፤ ጦቢትም አስቀድሞ ሰላምታ ሰጠው፤ እርሱም “መልካም ነገር እመኝልሃለሁ” ሲል መለሰለት። ጦቢትም “ከእንግዲህ ወዲህ ምን መልካም ነገር ማግኘት እችላለሁ? ዐይኖቼን አጥቻለሁ፤ የሰማይን ብርሃን ማየት አልችልም፥ ብርሃንን እንደማያዩ ሙታን በጨለማ እገኛለሁ፥ ሕያው ብሆንም ከሞቱት ጋር እቆጠራለሁ፥ ሰዎች ሲናገሩ ድምፃቸውን እሰማለሁ ነገር ግን አላያቸውም” አለ፤ መልአኩም “አይዞህ፥ በቅርቡ እግዚአብሔር ይፈውስሃል፤ አይዞህ” አለው። ጦቢትም “ልጄ ጦብያ ወደ ሜዶን መሄድ ይፈልጋል፤ የመንገድ ጓደኛው በመሆን ልትመራው ትችላለህን? ደሞዝህን እከፍልሃለሁ ወንድሜ።” አለው። እሱም “ከእርሱ ጋር እሄዳለሁ፤ መንገዶቹን ሁሉ አውቃቸዋለሁ፥ ወደ ሜዶን ብዙ ጊዜ ሄጄአለሁ፤ በሜዳዎቹና በተራራዎቹም አቋርጫለሁ፥ መንገዶቹንም ሁሉ አውቃቸዋለሁ” አለው። 11 ጦቢትም “ከየትኛው ቤተሰብና ከየትኛው ነገድ ነህ? እስቲ ንገረኝ ወንድሜ” አለው። 12 መልአኩም “ነገዴን ማወቅ ምን ይረባሃል?” አለው። ጦቢትም “የማን ልጅ እንደሆንክ እርግጠኛ መሆንና ስምህ ማን መሆኑን ማወቅ እፈልጋለሁ” አለው። 13 እርሱም “ስሜ አዛርያ ነው፥ ከዘመዶችህ አንዱ የሆነው የታላቁ አናንያ ልጅ ነኝ” አለው። 14 ጦቢትም “ወንድሜ ሆይ እንኳን በደኀና መጣህ፥ ስለ ቤተሰብህ እርግጡን ለማወቅ በመሻቴ አትቀየመኝ፥ ወንድማችን መሆንህ ከጥሩ ዘር መወለድህ አወቅሁ፤ የታላቁ የሸማይያ ሁለት ልጆች አናንያንና ናታንን አውቃቸዋለሁ፤ ከኔ ጋር ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር አብረን እንሰግድ ነበር። ከእምነታቸው ንቅንቅ አላሉም፤ ዘመዶችህ ደጐች ናቸው፥ ከመልካም ዘር ተወልደሃል፤ እንኳን ደኀና መጣህ” አለው። 15 ቀጥሎም እንዲህ አለው “ደሞዝህ አንድ ድራክማ በቀን እሰጥሃለሁ፥ በተጨማሪም ለሌላ ወጪህ እኩል ከልጄ ጋር እሰጥሃለሁ፥ ከልጄ ጋር ሂድ፤ 16 ከደሞዝህ ሌላም እጨምርልሃለሁ።” መልአኩም “ከእርሱ ጋር እሄዳለሁ፥ አትፍራ፤ በደኀና ሄደን በደኀና እንመለሳለን፤ መንገዱ አያሰጋም” አለው። 17 ጦቢትም “ተባረክ ወንድሜ” አለው። ልጁንም ጠራና “ልጄ ለመንገድ የሚያስፈልገውን አዘጋጅና ከወንድምህ ጋር ሂዱ፥ በሰማይ ያለ አምላክ በደኀና እዛ ያድርሳችሁ፥ በደኀናና በጤና ወደ እኔ ይመልሳችሁ፥ ልጄ መልአኩ ከእናንተ ጋር ይሂድ፥ ይጠብቃችሁም” አለው። ጦቢያ ከመሄዱ በፊት አባቱንና እናቱን ሳማቸው፤ ጦቢትም “መልካም መንገድ” አለው። 18 እናቱ ግን እያለቀሰች ጦቢትን እንዲህ አለችው “ለምንድነው ልጄን የላክኸው? በፊታችን ሲመላለስ የእጃችን ምርኩዝ እሱ አይደለምን? 19 ዋናው ጉዳይ ገንዘብ እንዳልሆነ ታውቃለህን? እንደ ልጃችንስ የከበረ ነውን? 20 ጌታ የሰጠን ሕይወት ለእኛ በቂያችን ነው።” 21 ጦቢትም “እህቴ ሆይ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አታስቢ፥ በደኅና ሄዶ በደኅና ይመለሳል፥ አንቺም በደኅና መመለሱን በዓይንሽ ታያለሽ፥ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አታስቢ፥ ስለ እነርሱም አትጨነቂ፤ 22 ደግ መልአክ ከርሱ ጋር ይሄዳል፤ ጉዞውም የተሳካ ይሆናል። በጤንነትና በደስታ ይመለሳል” አላት። |