1 ጠላት ከምትሆን ወዳጅ ሁን፤ የክፉ ስም ፍጻሜው ስድብና ውርደት ነውና፤ ምላሱ ሁለት የሆነ ኀጢአተኛ ሰውም እንዲህ ነው። 2 ከልቡናህ ባነቃኸውም ምክር ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤ አንበሳ ላምን እንደሚነጣጠቅ ሰውነትህን እንዳይነጥቋት። 3 ቅጠልህን ይበላብሃል፥ ፍሬህንም ታጣለህ፤ እንደ ደረቅ እንጨትም ይጥልሃል። 4 ክፉ ሰውነት ገንዘብ ያደረጋትን ሰው ታጠፋዋለች፤ ጠላቱንም በእርሱ የጨከነ ታደርገዋለች። እውነተኛና እውነተኛ ያልሆነ ጓደኝነት5 ልዝብ አንደበት ወንድማማችነትን ያበዛል፤ ልዝብ አፍም ወዳጅን ያበዛል። 6 ብዙ ሰዎች ወዳጆች ይሁኑህ፤ ነገር ግን ከብዙዎቹ አንዱ ምክርህን የምትገልጥለት ይሁን። 7 ወዳጅ ብታበጅ በችግርህ ወራት ወዳጅ አብጅ። ፈጥነህም እምነት አትጣልበት፤ 8 ለጥቂት ቀን የሚሆን ወረተኛ ወዳጅ አለና፤ በመከራህም ጊዜ ከአንተ ጋራ አይታገሥም። 9 ጠላት የሚሆንህና፥ የሚሰድብህ፥ ሰውረህ የሠራኸውን ኀጢአትህንም የሚገልጥብህ ወዳጅ አለ። 10 ስለ ማዕድህም የሚወድህ ወዳጅ አለ፤ እርሱም ከአንተ ጋራ አይኖርም፥ በተቸገርህም ጊዜ ይለይሃል። 11 ባለጸጋ በሆንህ ጊዜ እንዳንተ ይሆናል፤ ቤተ ሰብህንም ይገዛል። 12 ብትቸገር ግን እርሱ ባላጋራህ ይሆናል፤ እንዳታየውም ይሰወርሃል። 13 ከጠላቶችህ ራቅ፥ ወዳጆችህንም ተጠባበቃቸው። 14 የታመነ ወዳጅ እንደ ጸና አላባሽ አግሬ ጋሻ ነው፤ እርሱን ያገኘ ሰው ድልብ አገኘ። 15 ለታመነ ወዳጅ ለውጥ የለውም፤ ለደግነቱም ሚዛን የለውም። 16 የታመነ ወዳጅ የሕይወት መድኀኒት ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚፈሩ ያገኙታል። 17 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ወዳጅነቱን ያጸናል፤ ባልንጀራው እንደ እርሱ ይሆነዋልና። የጥበብ በረከት18 ልጄ ሆይ፥ በሕፃንነትህ ጥበብን ምረጣት፤ እስክታረጅም ድረስ ታገኛታለህ። 19 እንደሚያርስና እንደሚዘራ ሰው ወደ እርስዋ ሂድ፤ የተባረከ ፍሬዋንም ጠብቅ፤ ስለ እርስዋ በመሥራት ጥቂት ትደክማለህ፤ ነገር ግን ፈጥነህ ፍሬዋን ትበላለህ። 20 በሰነፎች ዘንድ ፈጽማ ጐፃጕፅ ናት፤ አእምሮ በሌለው ሰውም አታድርም። 21 የፈተና ድንጋይ አንሥተው በተሸከሙት ጊዜ እንዲከብድ፥ እንደዚሁ ትከብደዋለች፤ ፈጥኖም ይጥላታል። 22 ጥበብስ እንደ ስሟ ናት፤ ብዙ ሰዎችም የሚያውቋት አይደሉም። 23 ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ በምክሬም ጽና፤ ምክሬንም አታቃልል። 24 እግሮችህን ወደ ቀምበርዋ አግባ፤ ዛንጅርዋንም ባንገትህ እሰር። 25 ጫንቃህን ዝቅ አድርገህ ተሸከማት፤ በእግር ብረትዋም አትበሳጭ። 26 በፍጹም ነፍስህ ወደ እርሷ ተሰማራ፥ በፍጹም ኀይልህም መንገድዋን ጠብቅ። 27 ፍለጋዋን ተከተል፥ ፈልጋት፤ ታገኛታለህም። ያዛት፥ አትተዋትም። 28 በፍጻሜህም ዕረፍትን ታገኛለህ፤ ደስታም ይሆንሃል። 29 እግር ብረትዋም እንደ ጽኑ ጋሻ ይሆንልሃል፤ ዛንጅርዋም የክብር ልብስ ወደ መሆን ይመለስልሃል። 30 የዘለዓለም ወርቅ በእርሷ ዘንድ አለና፤ ማሰሪያዋም የሰማያዊ ሐር ጌጥ ይሆንሃል። 31 እንደ ክብር ልብስ ትለብሳታለህ፥ የደስታ ዘውድንም ታቀዳጅሃለች። 32 ልጄ ሆይ፥ ብልህ ትሆን ዘንድ ብትወድድ፥ ትማርም ዘንድ በልቡናህ ብትጨክን፥ 33 ትሰማ ዘንድ ብትወድም ታገሥ፤ ጆሮህንም ብታዘነብል ብልህ ትሆናለህ። 34 በብዙ ሽማግሌዎች ዘንድ ቁም፤ ከእነርሱም ዐዋቂ ሰው ብታይ ተከተለው። 35 የመጽሐፉን ነገር ሁሉ ፈጥነህ ስማ፤ የጥበብም ምሳሌ አይዘንጋህ። 36 ብልህ ሰው ብታይ ፈጥነህ ወደ እርሱ ሂድ፤ እግርህም በደጃፉ መድረክ ይመላለስ። 37 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዐስብ፤ መጻሕፍቱንም ሁልጊዜ አንብብ፥ እርሱም ልቡናህን ያጸናዋል፤ ጥበብንም ትወዳት ዘንድ ይሰጥሃል። |