ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የየዕለት የሕይወት መመሪያ 1 ገንዘብህን በከንቱ አትበትን፤ በቃኝም አትበል። 2 የሰውነትህን ፈቃድ አትከተል። 3 እኔ ኀይለኛ ነኝ፤ ማንስ ይችለኛል አትበል፥ እግዚአብሔር በቀልን ይበቀላልና። 4 ኀጢአት ሠርቼ ፍዳ አልተቀበልሁም አትበል፥ እግዚአብሔር ብዙ ዘመን ይታገሣልና። 5 ስለ ኀጢአትህ ንስሓ መግባትን አትፍራ። የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነው ኀጢአቴንም ይቅር ይለኛል እያልህ በኀጢአት ላይ ኀጢአትን አትጨምር። 6 ምሕረትም መቅሠፍትም ከእርሱ ዘንድ ይመጣልና፤ መቅሠፍቱም በኀጢአተኛ ሰው ላይ ይወርዳል። 7 ለእግዚአብሔር መገዛትን ቸል አትበል። ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ፤ ፍዳህ ከመቅሠፍት ጋራ በመጣብህ ጊዜ በመከራ ትጨነቃለህ። 8 በመከራህ ጊዜ አንተን ማዳን አይችልምና፤ ለዐመፃ ገንዘብ አትሳሳ። ራስን ስለ መግዛትና ግልጽ ስለ መሆን 9 ለሰው ሁሉ ምሥጢርህን አታውጣ። የወደድኸውንም ሁሉ አትከተል፤ ምላሱ ሁለት እንደ ሆነ ኀጢአተኛ አትሁን። 10 አንተስ በጥበብህ ጸንተህ ኑር፤ ቃልህም አንድ ይሁን። 11 ለመስማትም ፈጣን ሁን፤ ቃልን ለመመለስ ግን የዘገየህ ሁን። 12 የምትነግረው ካለህ ለባልንጀራህ ንገረው፤ ያለዚያ ግን እጅህን ባፍህ ላይ አድርግ። 13 መከበርህና መዋረድህ ከቃልህ የተነሣ ነው፤ የሰውም ውድቀቱ ከአንደበቱ የተነሣ ነው። 14 ሐሜተኛ አትሁን፥ በአንደበትህም አውታታ አትሁን፤ የሌባ እፍረቱ ጥቂት ነው። አንደበቱ ሁለት የሆነ ሰው ግን መከራው ጽኑ ነው። 15 በታላቁም በታናሹም ሰው ዘንድ ቸር ሆነህ ተገለጥ። |