ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ክፋትን አትሥራት፤ ክፉም አያገኝህም። 2 ከበደል ራቅ፥ እርሷም ራስዋ ካንተ ትርቃለች። 3 ሰባት እጥፍ አድርገህ እንዳትሰበስባት፥ በኀጢአት ትልም አትዝራ። 4 ከእግዚአብሔር መንግሥትን አትለምን፤ ከንጉሥም የክብር ዙፋን አትለምን። 5 በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ነኝ አትበል፤ በንጉሥም ዘንድ ብልህ ነኝ አትበል። 6 ዳኛ መሆንን አትውደድ፤ እነሆ፥ በደለኛውን ለመበቀል አትችልም ይሆናል፤ እነሆ፥ ለባለጸጋም ታደላ ይሆናል፤ በእውነት ሥራህም ላይ ኀጢአት ትሠራለህ። 7 ያገርህንም ሰው አትበድል፤ ራስህንም በወገኖችህ መካከል አታስት። 8 በአንዲቱም ቢሆን ከቅጣት አታመልጥምና፥ ሁለት ኀጢአት አንድ አድርገህ አትሥራ። 9 በመባዬ ብዛት እግዚአብሔር ኀጢአቴን ያስተሰርይልኛል፤ ለልዑል እግዚአብሔርም መባእ ከአገባሁ ይቅር ይለኛል አትበል። 10 በምትጸልይበት ጊዜ አትቸኩል፥ ምጽዋት መመጽወትንም አታቃልል። 11 የሚያሳዝን፥ ደስ የሚያሰኝም አለና፥ ባዘነ ሰው አትሳቅ። 12 በባልንጀራህ ሐሰትን ተግባር አታድርግ፤ በወዳጅህና በባልንጀራህም ላይ እንዲህ አታድርግ። 13 በምንም ሁልጊዜ ሐሰትን አትውደድ፥ ፍጻሜዋ ይጎዳሃልና። 14 በሽማግሌዎች መካከል ብዙ ቃል አትናገር፤ በአፍህ የተናገርኸውን ስእለትህን አትመልስ፥ ቃልህንም አትለውጥ። 15 የእጅህንም ሥራ አታቃልል፥ ፈጣሪህም የሚያበቅልልህን ቡቃያህን ቸል አትበል። 16 ብዙ ናቸው ብለህ ከኀጢአተኞች ጋር አንድ አትሁን። 17 ጥፋት እንደማትዘገይ ዐስብ፥ ሰውነትህን ፈጽመህ አዋርዳት፥ የኀጢአተኞች ፍዳቸው ትልና እሳት ነውና። 18 በእየነጋው ወዳጅ አትለውጥ፤ ስለ ቀይ ወርቅ ወዳጅህን አትጣ። 19 መወደዷ ከወርቅ ይወደዳልና ብልህና ደግ ሴትን አትጥላ። 20 በእውነት በሚገዛልህ ቤተ ሰብህ ላይ፥ ስለ አንተ ሰውነቱን አሳልፎ በሚሰጥ በምንደኛህም ላይ ክፉ ነገርን አታድርግ። 21 ብልህ ቤተ ሰብህን እንደ ራስህ ውደደው፤ ነጻ ታወጣውም ዘንድ ተስፋ ያደረገህን ዋጋውን አታጥፋበት። 22 ሁልጊዜ ከብትህን መፍቀድ አትተው፤ ከእነርሱ የሚጠቅምህን ወደ አንተ አቅርብ። 23 ልጆች ቢኖሩህ ምከራቸው፤ ከሕፃንነታቸው ጀምረህ ትሕትናን አስተምራቸው። 24 ሴቶች ልጆችም ቢኖሩህ ጠብቃቸው፤ አታስታቸው፥ አትሣቅላቸው፥ አታባብላቸውም። 25 ልጅህን አቅመ ሔዋን ስታደርስ አጋባት፥ ጠብቃት፥ ታላቅ ሥራንም ትፈጽማለህ፥ ከድካምም ታርፋለህ፥ ነገር ግን ለብልህ ሰው አጋባት። 26 እንደ ራስህ የምትወዳት ሚስት ብትኖርህ አትፍታት። 27 በፍጹም ልቡናህ አባትህን አክብረው፥ የእናትህንም ምጧን አትዘንጋ። 28 በእነርሱም ምክንያት እንደ ተወለድህ ዐስብ፤ ስላደረጉልህስ ፋንታ ምን ታደርግላቸዋለህ? 29 በፍጹም ሰውነትህ እግዚአብሔርን ፍራው፤ ካህናቱንም አክብራቸው። 30 በፍጹም ኀይልህም ፈጣሪህን ውደደው፤ የሚያገለግሉትንም አትተዋቸው። 31 እግዚአብሔርን ፍራው፤ የሚያገለግለውን ካህኑንም አክብረው፤ የታዘዘልህ ዕድሉንም ስጠው፤ ቀዳምያቱንና፥ ስለ ኀጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት፥ ወርቹንም፥ ማታና ጧትም የሚሠዋውን መሥዋዕት፥ መጀመሪያ የሚወለደውንም ከብት ስጠው። 32 በረከትህ ፍጽምት ትሆን ዘንድ እጅህን ለድሃ ዘርጋ። 33 ስጦታ በሕያው ሁሉ ፊት ጸጋ አለው፥ ስለ ሞተ ሰውም ምጽዋት መስጠትን አትተው። 34 ከሚያለቅሱ ሰዎችም አትለይ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅስ። 35 ሕመምተኛንም ሰው መጐብኘት ቸል አትበል፥ በዚህም ይወዱሃል። 36 በተናገርኸው ነገር ሁሉ ፍጻሜህን ዐስባት፥ ሁልጊዜም አትበድል። |