የአንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ የመጨረሻ ቀናት1 ንጉሥ አንጥዮኩስ በላይኞቹ ክፍለ ሀገር ይዘዋወር ነበር፤ በፋርስ አገር በሀብትም፥ በብርና በወርቅ የታወቀች ኤሊማይድ የምትባል ከተማ እንዳለች ስማ፤ 2 በመጀመሪያ በግሪካውያን ላይ የነገሠው የመቄዶንያው ንጉሥ የፊሊጶስ ልጅ እስክንድር የተዋቸው የወርቅ ጋሻዎችና የብረት ልብሶች፥ የጦር መሣሪያዎችም ያሉበት በጣም ሀብታም የሆነ ቤተ መቅደስ በዚያ እንዳለ ሰማ። 3 ወደዚያ ሄደ፥ ከተማዋን ይዞ ለመዝረፍ ፈለገ፤ ነገር ግን የከተማዋ ሰዎች ነገሩን ስለ ሰሙ አልተሳካለትም፤ 4 ውጊያ ሊገጥሙት ተነሡ፤ እርሱም ወደ ኋላ አፈገፈገ፤ እጅግ አዝኖ ወደ ባቢሎን ተመልሶ ለመሄድ ቦታውን ለቀቀ። 5 ወደ ይሁዳ አገር የሄዱት ወታደሮች መሸነፋቸው ነበር፤ አይሁዳውያን በጦር መሣሪያዎችና በስንቅ ካሸነፉቸው በፋርስ ተነገረው። 6 ከባድ ሠራዊት ይዞ የሄደው ሊስያስ በአይሁዳውያን ተሸንፎ ነበር፤ አይሁዳውያን በጦር መሣሪያዎችና በስንቅ ካሸነፉዋቸው ሠራዊቶች በወሰዱዋቸው ብዙ ምርኮዎች ተጠናክረው ነበር። 7 እንዲሁም አንጥዮኩስ በኢየሩሳሌም መሠዊያ ላይ ሠርቶ የነበረውን ርኩስ ነገር ገለባብጠውት ነበር፤ ቤተ መቅደሳቸውን እንደ ቀድሞው በረጅም ግንብ ከበውት ነበር፤ እንዲሁም የንጉሡን ከተማ ቤተሱርን ይዘው አጠናክረውት ነበር፤ 8 ንጉሡ ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ደንግጦና ታውኮ በአልጋው ላይ ወደቀ፤ ነገሮች እርሱ እንደፈለገው ስላልሆኑለት በትካዜ በሽታ ላይ ወደቀ። 9 በኀዘን ተውጦ በሽታው እየጠናበት ብዙ ቀኖች ቆየ፤ የሚሞት መሆኑም ታወቀው፤ 10 በዚያን ጊዜ ወዳጆቹን ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፥ “እንቅልፍ ከዐይኖቼ ርቋል፤ ሐሳብ ያስጨንቀኛል፤ 11 እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በዙሪያዬ ሊከበኝ፥ የመከራም ጎርፍ ሊያጥለቀልቀኝ እንደምን እንደቻለ አይገባኝም፤ በጣም ጀግና የተወደድኩም ነበርኩና። 12 አሁን ግን በኢየሩሳሌም ላይ የፈጸምኳቸው ክፉ ድርጊቶች ታወሱኝ፤ እዚያ የሚገኘውን የወርቅ ብር ዕቃዎች ሁሉ ወስጃለሁ፤ ያለ ምክንያት የይሁዳን አገር ሰዎች አስጨርሻለሁ። 13 ይህ ክፉ ነገር የደረሰብኝ በዚህ ምክንያት መሆኑን አወቅሁ፤ እነሆ በሰው አገር በትካዜ መሞቴ ነው”። የአምስተኛው የአንጥዮኩስ መተካት14 ከወዳጆቹ አንዱን ፊሊጶስን ጠርቶ በመላው መንግሥቱ ላይ ሾመው፤ 15 ልጁን አንጥዮኩስን እንዲያሳድግና አደራ በማለት አክሊሉን፥ ቀሚሱን፥ ማኀተሙን ሰጠው። 16 ንጉሥ አንጥዮኩስ በመቶ አርባ ዘጠኝ ዓመት ላይ በዚያን ቦታ ሞተ። 17 ሊሲያስ የንጉሡን ሞት በሰማ ጊዜ ከልጅነቱ የሳደገው የንጉሡን ልጅ አነገሠና ሰሙን ኤውጳጦር አለው። የኢየሩሳሌም ምሽግ በይሁዳ መቃቢስ ተከበበ18 የምሽጉ ሰዎች እስራኤላውያንን በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ዘግተውባቸው ሁልጊዜ በእርሱ ላይ ክፉ ሥራ ለመሥራትና አረማውያንን ለማጠናከር ይፈልጉ ነበር። 19 ይሁዳ እነርሱ ለመደምሰስ ፈለገ፤ እነርሱን ለመክበብና ለመውጋት ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ። 20 ሕዝቡም ተሰበሰበ፤ ምሽጉ ፊት ለፊት በመቶ ሐምሳ 163 ዓ.ዓ ከበባውና ውጊያው ተደረገ፤ የጦር መወርወሪያ መሣሪያዎችና ሌሎችም የጦር መኪናዎች ተዘጋጁ። 21 ግን ከተከበቡት አንዳንዶቹ ከበባውን ጥሰው መውጣት ችለዋል። ከእነርሱ ጋር አንዳንድ ከሐዲዎች እስራኤላውያን አብረው ተቀላቀሉ። 22 ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት “እውነተኛ ፈርድ ለመስጠትና የወንድሞቻችንን ደም ለመበቀል እስከ መቼ ነው የምትጠብቀው? 23 እኛ አባትህን ለማገልገልና ትእዛዙን ለመፈጸም፥ ሕጉንም ለመጠበቅ ደስተኞች ነበርን፤ 24 በዚህ የተነሣ ከወገኖቻችን ጋር ተቆራርጠናል፤ በእኛ መካከል የነበሩትን ሰዎች አግኝተው ገድለዋል፤ ቤተሰቦቻችንን፥ ንብረቶቻችንንም ዘርፈዋል። 25 እጃቸውን ያነሡት በእኛ ላይ ብቻ አይደለም፤ በግዛቶችህም ሁሉ ላይ ነው። 26 ይኸውና መቅደሱንና ቤተሱርን አጠናክረው መሽገዋል። 27 አሁን ቶሎ ብለህ ካልያዝሃቸው (ካላቆምሃቸው) እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ልታቆማቸውም የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርሳለህ”። የአምስተኛው አንጥዮኩስና የሊስያስ ዘመቻ የቤተ ዘካሪያስ ጦርነት28 ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ ተቆጣና ወዳጆቹን ሁሉ የእግረኛና የፈረሰኛ ጦር አለቆችን፥ አማካሪዎችን ሰበሰበ። 29 ከሌሎች መንግሥታትና ከሜድትራኒያን ደሴቶችም ቅጥረኛ ወታደሮች መለመለ። 30 የዳበረ የጦርነት ልምድ ያላቸው የእረኛ ወታደሮቹ ቍጥር እስከ መቶ ሺህ፥ ፈረሰኛ ጦር ሃያ ሺህ፥ ዝሆኖች ደግሞ ሠላሳ ሁለት ነበሩ። 31 በኤዱሚያስ በኩል መጥተው ቤተሱርን ከበቡ፤ በጦር ተሽከርካሪዎች እየተረዱ ብዙ ጊዜ ወጓት፤ ግን የተከበቡት መውጫ አበጅተው እሳት ለቀቁባትና በጀግንነት ተዋጉ። 32 በዚያን ጊዜ ይሁዳ ከምሽጉ ወጥቶ በንጉሡ ሰፈር ፊት ለፊት በቤተ ዘካርያስ ቦታውን ያዘ። 33 ንጉሡ በማለዳ ተነሥቶ ሠራዊቱን ባንድ ጊዜ ወደ ቤተዘካርያስ መንገድ ላይ አስወጣ፤ ወታደሮቹም ለውጊያ ተሰለፉ፤ መለከትንም ነፉ። 34 ዝሆኖቹን ለውጊያ ለማነሣሣት የወይንና የእንጆሪ ጭማቂ አቀረቡላቸው። 35 እንስሶቹ በእግረኛ ጦር መካከል ተከፋፈሉ፤ በእያንዳንዱ ዝሆን አጠገብ የብረት ልብስ የለበሱና የራስ ቁር ያደረጉ ወታደሮች ተሰልፈው ቆሙ፤ እንዲሁም አምስት መቶ ምርጥ ፈረሰኞች በእያንዳንዱ ዝሆን ጐን ተሰለፉ። 36 እነዚህ ወታደሮች የዝሆኑን እንቅስቃሴ አስቀድመው በመመልከት ከቶ ሳይለዩት በሁሉ ቦታ ይከተሉት ነበር።፥ 37 በእያንዳንዱ ዝሆን ላይ በጠፍር ጥብቅ ተደርጐ የታሰረ ጠንካራ የእንጨት ቤት እንደ መከላከያ ምሽግ ሆኖ ተሠርቶለት ነበር። በውስጡም ተመድበው የሚያገለግሉ ሶስት ተዋጊ ወታደሮችና አንድ የዝሆን ጠባቂ ይገኛሉ። 38 ንጉሡ የቀረውን ፈረሰኛ ሠራዊት ጦሩን እንዲያነቃቃና እንዲጠብቅ በሠራዊቱ ጐንና ጐን አሰለፈው። 39 በወርቅና በናስ የተሠሩ ጋሻዎች ላይ ፀሐይ ብልጭ ባለ ጊዜ ተራራዎቹ በሩ፥ እንደነደደ ችቦ ተንቦገቦጉ። 40 የንጉሡ አንደኛው ክፍለ ጦር ወደ ተራራው ጫፎች ላይ ተሰማራ፤ የቀረው ክፍል ወደ ዝቅተኛው ቦታ ሄደ፤ በጥንቃቄና በሥነ ሥርዓት ይሄዱ ነበር። 41 የእነዚህን የብዙ ወታደሮች ጫጫታና የእግሮቻቸውን ድምፅ፥ የሠራዊታቸውንና የመሣሪያዎቻቸውን ቅጭልጭልታ በሰሙ ጊዜ ሰዎች ሁሉ ደነገጡ፤ ይህ ሠራዊት በእውነቱ እጅግ በጣም ብዙና ብርቱ ነበር። 42 ይሁዳና ሠራዊቱ ውጊያውን ለመጀመር ወደ ፊት ሄዱ፤ ከንጉሡ ሠራዊት ስድስት መቶ ሰዎች ሞቱ። 43 አዋራን ተብሎ የሚጠራው ኤልዓዛር የንጉሡ የጦር ልብስ የተደረበበትና 44 በቁመቱ ከሌሎቹ ዝሆኖች ሁሉ ከፍ ያለ አንድ ዝሆን በማየቱ የማይሞት ስም ለማትረፍ ብሎ ራሱን ሠዋ፤ 45 ይህ ሰው በግራና በቀኝ ያሉትን ወታደሮች እየጨፈጨፈ በሠራዊቱ መካከል ወደ ዝሆኑ በድፍረት እየተንደረደረ ሄደ፤ ጠላቶቹም ወዲያና ወዲህ ገለል ብለው አሳለፉት። 46 እርሱም ወደ ዝሆኑ ሥር ገብቶ ዝሆኑን በታች በኩል በኃይል ወጋውና ገደለው፤ ዝሆኑ ኤልዓዛር ላይ ወደቀና ኤልዓዛር ወዲያውኑ ሞተ፤ 47 አይሁዳውያን የንጉሡን ጦር ኃይል ብርታት በማየት ወደ ኋላ አፈገፈጉ። የቤተሱር መያዝና የጽዮን ተራራ በሶሪያውያን መከበብ48 የንጉሡ ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ውጭ ሊገጥማቸው ተንቀሳቀሰ፤ ንጉሡም የይሁዳን ምድርና የጽዮንን ተራራ ከበበ። 49 ከተማዋን ለቀው የሚወጡ የቤተሱር ሰዎች ንጉሡ ሰላምን እንደሚሰጥ ቃል ገባ፤ ከተማዋ ዓመታዊውን የእረፍት ጊዜ የምታሳልፍበት ስለ ነበር ከበባውን ተቋቁማ የምግብ አቅርቦትን ልታሟላ አልቻለችም ነበር። 50 ንጉሡ ቤተሱርን ያዘ፤ እዚያም ጠባቂ ወታደሮች አደረገበት። 51 ለብዙ ቀኖች ቤተ መቅደሱን ከበበ፤ የድንጋይ መወርወሪያ መሣሪያዎችና መዘውሮች፥ እሳትና ጦር ወርዋሪ መሣሪያዎች፥ ቀስት መወርወሪያዎችና ወንጭፎች ከእዚያ አደረገ። 52 የተከበቡት ሰዎች የራሳቸውን ተሽከርካሪዎች በመስራት የመከላከል ችሎታቸውን አጠናከሩ። 53 ነገር ግን በመጋዘናቸው የሚበላ አልነበራቸውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ዘመኑ ሰባተኛው የዕረፍት ዓመት በመሆኑና ከአረመኔዎች መካከል ወደ ይሁዳ አገር በመሄድ የተጠጉት እስራኤላውያን የመጨረሻውን ስንቅ በልተው አጠናቀው ስለ ነበር ነው 54 በረሃብ አደጋ ላይ ስነበሩ በቤተ መቅደሱ ጥቂት ሰዎች ብቻ ትተው ሌሎቹ ወደየቦታው ተበታተኑ። ንጉሡ ለአይሁዳውያን የሃይማኖት ነጻነት ሰጠ55 ልጁን አንጥዮኩስ (5 ኛውን) እንዲያሳድግለትና ለመንገሥ እንዲያበቃው በንጉሥ አንጥዮኩስ (4 ኛው) የተሾመው ፊሊጶስ 56 ከንጉሡ ጋር ዘምተው ከነበሩት ወታደሮች ጋር ከፋርስና ከምድያም ተመልሶ መምጣቱንና የሁሉም ነገር የበላይ አስተዳዳሪ መሆን መፈለጉን 57 ሊስያስ በሰማ ጊዜ ለመሄድ በፍጥነት ተዘጋጀ፤ ንጉሡንና የሠራዊቱን መሪዎች፥ ሰዎቹንም ምግባችንም እያለቀ ሄደ፤ ይህ የከበብነው ቦታ በጣም የተጠናከረ ነው፤ የመንግሥቱ አስተዳደር ጉዳይ ኃላፊነቱ የወደቀው እኛ ላይ ነው። 58 አሁን ቀኝ እጃችንን ወደ እነዚህ ሰዎች ዘርግተን ከእርሱ ጋርና ከሕዝባቸውም ሁሉ ጋር ሰላም እናድርግ፤ 59 እንደ ቀድሞው በልማዳቸው መሠረት እንዲያደርጉ እንፍቀድላቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ የተቆጡትና ይህን ሁሉ ያደረጉት ባህላቸውን ስለደመሰስንባቸው ነው በማለት ተናገረ። 60 ይህ ንግግር ንጉሡንና ሹማምንቱን ደስ አሰኘ፤ ስለዚህ ሊስያስ ሰላም እናድርግ ባለው መሠረት ንጉሡ ወደ አይሁዳውያን የሰላም ቃል ላከ፤ እነርሱም እሺ ብለው ተቀበሉ። 61 ንጉሡና ሹማምንቱም ጉዳዩን በመሐላ ካጸደቁት በኋላ የተከበቡት ከምሽጉ እንዲወጡ ተፈቀደላቸው። 62 ንጉሡ ወደ ጽዮን ተራራ ሄዶ (ገብቶ) ቦታው ምን ያህል የማይደፈር መሆኑን እንደተመለከተ ምሽጐችን ካየ በኋላ መሐላውን በማፍረስ መካበቢውን ግንብ እንዲያፈርሱ ትእዛዝ ሰጠ። 63 ከዚህ በኋላ በፍጥነት ሄደ፤ ወደ አንጾኪያም ተመለሰ፤ እዚያ ፊሊጶስን የከተማዋ ሹም ሆኖ አገኘው፤ ውጊያ ገጠመውና ከተማዋን በኃይል ወሰደበት። |