ዘካርያስ 13:7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፣ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍ ሆይ፤ በእረኛዬ፣ በቅርብ ወዳጄ ላይ ንቃ! እረኛውን ምታ፣ በጎቹም ይበተናሉ፤ እኔም ክንዴን ወደ ታናናሾቹ አዞራለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በጎቹም እንዲበተኑ እረኛውን ምታ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ አዞራለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ሰይፍ ሆይ! ተባባሪዬ በሆነው በእረኛዬ ላይ ንቃ! በጎቹ ይበተኑ ዘንድ እረኛውን ምታ! እኔም በታናናሾቹ ላይ እጄን አነሣለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፥ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ። |
እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ አግልሻለሁ፤ ዝገትሽንም አነጻለሁ፤ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ፤ ዐመፀኞችን አጠፋለሁ፤ ሕገ ወጦችንም ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ ትዕቢተኞችንም አዋርዳለሁ።
በዚያም ቀን እግዚአብሔር በፈጣኑ እባብ ደራጎን ላይ፥ በክፉውም እባብ ደራጎን ላይ ልዩ፥ ታላቅና ብርቱ ሰይፍን ያመጣል። በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድለዋል።
ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤
“አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ሰይፍ ሰይፍ ለመግደል ተመዝዞአል፤ ጨርሶም ያርድ ዘንድ ተሰንግሎአል በል።
ለእስራኤልም ምድር እንዲህ በል፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፤ ሰይፌንም ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፤ ጻድቁንና ኃጥኡን ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ።
“ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል።
አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፥ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።
እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፥ እነርሱም ይኖራሉ፥ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።
እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፣ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፣ መንጋውንም ጠበቅሁ።
“እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፤ ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” የሚል ነው።
ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።
ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ አህያ የሚፈጭበት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢሰጥም በተሻለው ነበር።
በማግሥቱም ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ የዓለሙን ኀጢኣት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን።
እያንዳንዳችሁ በየቦታዉ የምትበታተኑበት፥ እኔንም ብቻዬን የምትተዉበት ጊዜ ይደርሳል፤ ደርሶአልም፤ እኔ ግን ብቻዬን አይደለሁም፤ አብ ከእኔ ጋር ነውና።
እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት።
እኛንስ ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን መርገም በመሸከሙ ከኦሪት መርገም ዋጅቶናል፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው።”
ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
እንዲሁም “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊላደልፊያም ወደ ሎዲቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ፤” አለኝ።
ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።