ዘካርያስ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ከኃጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል። 2 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፣ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። 3 ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ፦ አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል፣ ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል። 4 በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፣ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም። 5 እርሱ ግን፦ ከታናሽነቴ ጀምሮ ባሪያ ሆኜ ነበርሁና ገበሬ ሰው ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም ይላል። 6 ሰውም፦ ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቁስል ምንድር ነው? ይለዋል። እርሱም፦ በወዳጆቼ ቤት የቈሰልሁት ቍስል ነው ይላል። 7 ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፣ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ። 8 በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፣ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል። 9 ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፣ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፣ እኔም፦ ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፣ እርሱም፦ እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል። |