2 ቆሮንቶስ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ምድራዊና ሰማያዊ ቤት 1 በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። 2 ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን። 3 ከለበስነውም በኋላ ዕራቍታችንን የምንገኝ አይደለንም። 4 በዚህ ቤት ውስጥ ሳለንም ከከባድነቱ የተነሣ እጅግ እናዝናለን፤ ነገር ግን ሟች በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ሌላ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንወድም። 5 ለዚህም ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ ሰጠን። 6 እንግዲህ ሁልጊዜ እመኑ፥ ጨክኑም፤ በዚህ ሥጋ ሳላችሁም እናንተ እንግዶች እንደ ሆናችሁ ታውቃላችሁ፤ ከሥጋችሁም ተለይታችሁ ወደ ጌታችን ትሄዳላችሁ። 7 በእምነት እንኖራለን፤ በማየትም አይደለም። 8 ታምነናል፤ ይልቁንም ከሥጋችን ተለይተን ወደ ጌታችን እንሄዳለንና ደስ ይለናል። 9 አሁንም ብንኖርም፥ ብንሞትም እርሱን ደስ ለማሰኘት እንጥራለን። 10 መልካም ቢሆን፥ ክፉም ቢሆን በሥጋችን እንደ ሠራነው ዋጋችንን እንቀበል ዘንድ፥ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለንና። ስለ መምህራን 11 እግዚአብሔርን መፍራት ዐውቀን ሰዎችን እናሳምናለን፤ ለእግዚአብሔር ግን እኛ የተገለጥን ነን፤ እንዲሁም በልቡናችሁ የተገለጥን እንደ ሆን እንታመናለን። 12 በዚህ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለም፤ ነገር ግን እኛ እንደምንመካባችሁ፥ እናንተም በእኛ እንድትመኩ፥ ከልብ ሳይሆን ለሰው ይምሰል በሚመኩ ሰዎች ዘንድ መልስ እንዲሆናችሁ ምክንያትን እንሰጣችኋለን። 13 እኛ ሰነፎች ብንሆንም፥ ስንፍናችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ዐዋቂዎች ብንሆንም ዐዋቂነታችን ለእናንተ ነው። 14 የክርስቶስ ፍቅር በዚህ አሳብ እንድንጸና ያስገድደናል፤ ሁሉ ፈጽመው ስለ ሞቱ አንዱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና። 15 በሕይወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ። 16 ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ በሥጋ የምናውቀው የለም፤ ክርስቶስንም በሥጋ ብናውቀው አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ የምናውቀው አይደለም። 17 አሁንም በክርስቶስ የሆነው ሁሉ አዲስ ፍጥረት ነው፤ የቀደመውም አለፈ፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆነ። ስለ ማስታረቅ መልእክት 18 ነገር ግን ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ከአስታረቀን፥ የማስታረቅ መልእክትንም ከሰጠን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 19 ኀጢአታቸውን ይቅር ብሎ በደላቸውንም ሳያስብ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለሙን ከራሱ ጋር አስታርቆአልና፤ የዕርቅ ቃሉንም በእኛ ላይ አደረገ፤ የይቅርታውንም መልእክት ሰጠን። 20 እኛስ በክርስቶስ አምሳል እንለምናለን፤ እግዚአብሔርም በእኛ መጽናናትን ይሰጣችኋል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኋለን። 21 ኀጢአት የሌለበት እርሱ እኛን ለእግዚአብሔር ያጸድቀን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን እንደ ኃጥእ አድርጓልና። |