ገላትያ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የገላትያን ሰዎች ስለ መገሠጹ 1 እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ? እርሱም እንዲሰቀል አስቀድሞ የተጻፈለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2 በእናንተ ዘንድ ይህን ብቻ ላውቅ እወድዳለሁ፤ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት? 3 እንዲህን ሰነፎች ናችሁን? የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከጀመራችሁ በኋላ የሥጋን ሕግ ልትሠሩ ትመለሳላችሁን? 4 ይህን ያህል መከራ ተቀብላችሁ፥ ለከንቱ አደረጋችሁት። 5 እርሱ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጣችሁ፥ ኀይልንም የሚያደርግላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት ነው? ስለ አብርሃም እምነትና ተስፋው 6 አብርሃም በእግዚአብሔር እንደ አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ እንደ ተቈጠረለት፥ 7 እንግዲህ ያመኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ታውቃላችሁ። 8 እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቃቸው መጽሐፍ አስቀድሞ ገልጦአልና፤ አሕዛብም ሁሉ በእርሱ እንዲባረኩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋ ሰጠው። 9 አሁንም የሚያምኑ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። 10 በኦሪት ሕግ ያሉ ሁሉ በእርግማን ውስጥ ይኖራሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በዚህ በኦሪት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ የማይፈጽምና የማይጠብቅ ርጉም ይሁን።” 11 የኦሪትን ሥራ በመሥራትስ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደማይጸድቁ ይታወቃል፤ “ጻድቅ ግን በእምነት ይድናል” ተብሎ ተጽፎአል። 12 ኦሪትስ ሠርቶ የፈጸመ ይኖርበታል እንጂ በእምነት የሚያጸድቅ አይደለም። 13 እኛንስ ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን መርገም በመሸከሙ ከኦሪት መርገም ዋጅቶናል፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው።” 14 እኛ በክርስቶስ አምነን የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ እንድናገኝ የአብርሃም በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አሕዛብ ይመለስ ዘንድ። ስለ ኦሪትና ስለ ተስፋው 15 ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እንናገራለን፤ ሰውም እንኳን የጸናውን ኪዳን አይንቅም አይጨምርበትምም። 16 እግዚአብሔርም ለአብርሃም፥ “ለአንተና ለዘርህ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፤ ለብዙዎች እንደሚናገር አድርጎ ለአንተና ለዘሮችህ አላለውም፤ ለአንድ እንደሚናገር አድርጎ፥ “ለዘርህ” አለው እንጂ ይኸውም ክርስቶስ ነው። 17 እንግዲህ እንዲህ እላለሁ፦ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ይህ ኪዳን ጽኑዕ ነው፤ ከዚህም በኋላ በአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኦሪት መጣች፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል አይደለም። 18 መውረስ የኦሪትን ሕግ በመሥራት ከሆነ እንግዲህ በሰጠው ተስፋ አይደለማ፤ እነሆ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋውን ሰጠው። 19 ታዲያ ኦሪት ለምን ተሠራች? ኦሪትስ ኀጢአትን ታበዛት ዘንድ፥ ተስፋ ያደረገለት ያ ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ በመላእክት በኩል በመካከለኛው እጅ ወረደች። 20 መካከለኛው ግን ማንም አይደለም፤ አንድ እግዚአብሔር ነው እንጂ። 21 እንግዲህ ኦሪት እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል መጣችን? አይደለም፤ ማዳን የሚቻለው ሕግ ተሠርቶ ቢሆንማ፥ በእውነት በዚያ ሕግ ጽድቅ በተገኘ ነበር። 22 ነገር ግን ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ይሆን ዘንድ፥ ያመኑትም ያገኙት ዘንድ፥ መጽሐፍ ሁሉን በኀጢአት ዘግቶታል። ስለ ሃይማኖት መምጣት 23 እምነት ሳይመጣ ኦሪት ጠበቀችን፤ ወደሚመጣውም እምነት መራችን። 24 እንግዲህ ኦሪት በእርሱ በማመን እንጸድቅ ዘንድ ወደ ክርስቶስ መሪ ሆነችን። 25 እንግዲህ እምነት ከመጣች መሪ አንሻም። 26 በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናልና። 27 በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል። 28 በዚህም አይሁዳዊ፥ ወይም አረማዊ የለም፤ ገዢ፥ ወይም ተገዢ የለም፤ ወንድ፥ ወይም ሴት የለም፤ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁና። 29 ለኢየሱስ ክርስቶስ ከሆናችሁም እንግዲህ ተስፋውን የምትወርሱ የአብርሃም ዘር እናንተ ናችሁ። |