ኤርምያስ 47 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት 1 ፈርዖንም ጋዛን ሳይመታ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ ውኃ ከሰሜን ይነሣል፥ የሚያጥለቀልቅም ፈሳሽ ይሆናል፤ በሀገሪቱና በመላዋ ሁሉ፥ በከተማዪቱና በሚኖሩባትም ላይ ይጐርፋል፤ ሰዎቹም ይጮኻሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ። 3 ከኀይለኞች ፈረሶች ከኮቴያቸው መጠብጠብ ድምፅ፥ ከሰረገሎቹም መሽከርከር፥ ከመንኰራኵሮቹም መትመም የተነሣ አባቶች በእጃቸው ድካም ምክንያት ወደ ልጆቻቸው አይመለሱም። 4 ይህም የሚሆነው ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ታጠፋ ዘንድ፥ ጢሮስንና ሲዶናን የቀሩትንም ረዳቶቻቸውን ታጠፋ ዘንድ ስለምትመጣው ቀን ነው፤ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንንና በከፍቶር ደሴት የቀሩትን ያጠፋልና። 5 ቡሀነት በጋዛ ላይ መጥቶአል፤ አስቀሎና ጠፋች፤ የዔናቅ ቅሬታዎች ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ገላችሁን ትነጫላችሁ? 6 አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ! ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ፤ ጸጥ ብለህም ዕረፍ። 7 እግዚአብሔር በአስቀሎናና በባሕር ዳር በቀሩትም ቦታዎች ላይ ትእዛዝ ሰጥቶአልና፥ በዚያም አዘጋጅቶታልና እንዴት ዝም ትላለህ? በዚያ ትነሣለህ። |