መዝሙር 95:1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኑ፤ ደስ እያለን ለእግዚአብሔር እንዘምር፤ በድነታችንም ዐለት እልል እንበል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኑ፥ በጌታ ደስ ይበለን፥ ለመዳናችን ዓለት እልል እንበል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኑ፤ እግዚአብሔርን በመዝሙር እናመስግን! ለመዳናችን አምባም የድል እልልታ እናስተጋባለት! |
በዚያ ጊዜም ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለእግዚአብሔር እንዘምራለን፤ በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፥ “ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና።”
የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ሰዎች ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የዚያችን ምድር ምርኮኞች ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።
ያዕቆብ በላ፤ ጠገበም፤ የተወደደውን ጥጋብ አቀናጣው፤ ሰባ፥ ወፈረ፥ ሰፋ፤ የፈጠረውንም እግዚአሔርን ተወ፤ ከሕይወቱ ከእግዚአብሔርም ራቀ።
በጥበብ ሁሉ እንድትበለጽጉ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ይጽና፤ በመንፈስም ራሳችሁን አስተምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝሙርንና ምስጋናን፥ የቅድስና ማሕሌትንም በልባችሁ በጸጋ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።
“ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ! የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፤ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፤” እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።
እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውሃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤” እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።