ኤፌሶን 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔርን መምሰል 1 እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ። 2 ክርስቶስ እንደ ወደዳችሁ፥ ራሱንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ የሚሆን መሥዋዕትና ቍርባን አድርጎ እንደ ሰጠላችሁ በፍቅር ተመላለሱ። 3 ነገር ግን ለቅዱሳን እንደሚገባቸው፥ ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም ቅሚያ አይሰማባችሁ። 4 የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ ማመስገን ይሁን እንጂ። 5 ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ። 6 በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና። 7 እንግዲህ አትምሰሉአቸው። 8 ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ። 9 የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና። 10 እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ። 11 የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ። 12 በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና። 13 ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። 14 “የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። 15 እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። 16 ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። 17 ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። 18 መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። 19 መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። 20 ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ። ስለ ትሕትናና የቤተ ሰብእ አመራር 21 እግዚአብሔርን በመፍራት ለባልንጀሮቻችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። 22 ሴቶችም ለጌታችን እንደሚታዘዙ ለባሎቻቸው ይታዘዙ። 23 ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደ ሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና። 24 ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ፥ እንዲሁም ሴቶች ለባሎቻቸው በሁሉ ይታዘዙ። 25 ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት፥ ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደ ሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ። 26 በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ፥ 27 የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኵሰት እንዳያገኝባት፥ ቤተ ክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ፤ 28 እንዲሁም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ይውደዱ፤ ሚስቱንም የወደደ ራሱን ወደደ። 29 ከቶ ሥጋውን መጥላት የሚቻለው የለም፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መገባት መግቡ፤ ጠብቁም። 30 እኛ የአካሉ ሕዋሳት ነንና። 31 “ስለዚህም ወንድ አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ።” 32 ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ። 33 እንግዲያስ እናንተም ሁላችሁ እንዲሁ ሚስቶቻችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ፥ ሴትም ባልዋን ትፍራው። |