1 ቆሮንቶስ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በእምነት ስለ አለመውደቅ 1 ወንድሞቻችን ሆይ፥ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ። 2 ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው። 3 ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። 4 ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ። 5 እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሁሉም ደስ አላለውም፤ ብዙዎቹ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። 6 እነርሱ እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ ክፉ እንዳንመኝ እነርሱ ለእኛ ምሳሌ ሆኑልን። 7 “አሕዛብ ተቀመጡ፤ ይበሉና ይጠጡም ጀመር፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንደ አመለኩ ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። 8 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ፥ በአንድ ቀንም ሃያ ሦስት ሺህ ሰዎች እንደ ወደቁ አንሴስን። 9 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እግዚአብሔርን እንደ ተፈታተኑት፥ ነዘር እባብም እንደ አጠፋቸው እግዚአብሔርን አንፈታተን። 10 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጐራጐሩበት፥ በመቅሠፍትም እንደጠፉ አናንጐራጕር። 11 እነርሱን ያገኛቸው ይህ ሁሉ ነገር በኋላ ዘመን ለምንነሣው ለእኛ ትምህርትና ምክር ሊሆነን ምሳሌ ሆኖ ተጻፈ። 12 አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13 በሰው ላይ እንደሚደርሰው ያለ ፈተና ነው እንጂ ሌላ ፈተና አያገኛችሁም። በምትችሉት መከራ ነው እንጂ በማትችሉት መከራ ትፈተኑ ዘንድ ያልተዋችሁ እግዚአብሔር የተመሰገነ ነው፤ እርሱም ከፈተና ትድኑ ዘንድ በመከራ ጊዜ ይረዳችኋል። ከጣዖታት ስለ መራቅ 14 ወንድሞች! አሁንም ጣዖት ከማምለክ ሽሹ። 15 ለዐዋቂዎች እንደሚነገር እነግራችኋለሁ፤ ትክክለኛውንም እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። 16 ይህ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር አንድ አይደለምን? የምንፈትተው ይህስ ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር አንድ አይደለምን? 17 ኅብስቱ አንድ እንደ ሆነ እንዲሁ እኛም ብዙዎች ስንሆን አንድ አካል ነን፤ ሁላችን ከአንድ ኅብስት እንቀበላለንና። 18 እስራኤል ዘሥጋን ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን ይበላሉ፤ ከመሠዊያውም ጋር አንድ ይሆኑ አልነበረምን? 19 እንግዲህ ምን እንላለን? ለጣዖታት የሚሠዋ መሥዋዕት ከንቱ ነው፤ ጣዖቶቻቸውም ከንቱ ናቸው። 20 አሕዛብም የሚሠዉ ለአጋንንት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም፤ ነገር ግን የአጋንንት ተባባሪዎች እንድትሆኑ አልፈቅድላችሁም። 21 የእግዚአብሔርን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ አንድ አድርጋችሁ መጠጣት አትችሉም፤ የእግዚአብሔርን ማዕድና የአጋንንትንም ማዕድ በአንድነት ልትበሉ አትችሉም። 22 እንግዲህ እግዚአብሔርን እናስቀናውን? በውኑ እኛ ከእርሱ እንበረታለን? 23 ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። 24 ለባልንጀራችሁ እንጂ ለራሳችሁ አታድሉ። 25 ደግሞም በሥጋ ገበያ የሚሸጡትን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ። 26 “ምድር በመላዋ የእግዚአብሔር ናትና።” 27 ያላመነ ሰው ቢጠራችሁ፥ ልትሄዱም ብትወዱ ያቀረቡላችሁን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ። 28 እንግዲህ “ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ያላችሁ ቢኖር ግን፥ ስለ ነገራችሁና ባልንጀራችሁም የሚጠራጠር ስለሆነ አትብሉ። 29 ነጻነታችሁን እንዳይነቅፉአት አስረድተዋችኋልና። 30 በጸጋ ብበላ ግን በነገሩ ስለማመሰግን ለምን ይነቅፉኛል። 31 ብትበሉም፥ ብትጠጡም የምታደርጉትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። 32 ለአይሁድም፥ ለአረማውያንም፥ ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ያለ ማሰናከል አርአያ ሁኑአቸው። 33 እኔም ሁሉን በሁሉ ነገር ደስ እንዳሰኝ ይድኑ ዘንድ የብዙዎችን ተድላ እሻለሁ እንጂ የራሴን ተድላ የምሻ አይደለሁምና። |