መዝሙር 107 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 ልቤ ጽኑዕ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑዕ ነው፤ አመሰግናለሁ እዘምራለሁም። 2 ክብሬም ይመለስልኛል፥ በበገናና በመሰንቆ እነሣለሁ፤ ማልጄም እነሣለሁ፤ 3 አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ በወገኖችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤ 4 ምሕረትህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና። 5 እግዚአብሔርም በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ክብሩም በምድር ሁሉ ላይ ነው። 6 ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም። 7 እግዚአብሔር በመቅደሱ ተናገረ፥ ደስ ይለኛል፥ ሰቂማንም እካፈላለሁ፥ የሸለቆ ቦታዎችን እሰፍራለሁ። 8 ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤ 9 ካህን ሞዓብም ተስፋዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤምም ይገዙልኛል። 10 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል? 11 አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላካችን ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም። 12 በመከራችን ረድኤትን ስጠን፤ በሰውም መታመን ከንቱ ነው። 13 በእግዚአብሔር ኀይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል። |