መዝሙር 95 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 ኑ፤ እግዚአብሔርን በመዝሙር እናመስግን! ለመዳናችን አምባም የድል እልልታ እናስተጋባለት! 2 ወደ ፊቱ ቀርበን እናመስግነው፤ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል! 3 እግዚአብሔር ታላቅ ንጉሥ ነው፤ በሌሎች አማልክት ሁሉ ላይም ንጉሥ ነው። 4 የመሬት ጥልቀቶች በመዳፉ ውስጥ ናቸው፤ የተራራ ጫፎችም የእርሱ ናቸው። 5 እርሱ የፈጠረው ስለ ሆነ ባሕር የእርሱ ነው፤ የብስንም የፈጠሩ እጆቹ ናቸው። 6 ኑ፤ ዝቅ ብለን እንስገድ! በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክ! 7 እርሱ አምላካችን ነው፤ እኛም እርሱ የሚጠነቀቅልን ሕዝቦቹና የሚያሰማራን መንጋዎቹ ነን፤ ስለዚህ ዛሬ እንዲህ ሲል የሚናገረውን አድምጡ፦ 8 “በዚያ በበረሓ ቦታ፥ በመሪባና በማሳ የቀድሞ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት እልኸኞች አትሁኑ። 9 እነርሱ ያደረግኹላቸውን ድንቅ ነገር ቢያዩም እንኳ በዚያ ተፈታተኑኝ፤ ተገዳደሩኝም። 10 ያን ሕዝብ አርባ ዓመት ሙሉ ተጸየፍኩት፤ ‘እነርሱም ልባቸው የባከነና እኔን መከተል ያላወቁ ሰዎች ናቸው’ አልኩ። 11 ተቈጥቼም ‘ዕረፍት ወደምታገኙባት ምድር ከቶ አትገቡም’ ብዬ ማልኩ።” |