መዝሙር 100 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ምሕረትንና ፍርድን እዘምርልሃለሁ። 2 እዘምራለሁ፥ ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ፤ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ። 3 በዐይኔ ፊት ክፉ ነገርን አላኖርሁም፤ ዐመፃ የሚያደርጉትን ጠላሁ። 4 ጠማማ ልብም አልተከተለኝም፤ ክፉ ከእኔ በራቀ ጊዜ አላወቅሁም። 5 ባልንጀራውን በስውር የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤ በዐይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም። 6 ከእኔ ጋር አኖራቸው ዘንድ ዐይኖቼ ወደ ምድር ምእመናን ናቸው፤ በንጹሕ መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል። 7 ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ መካከል አይኖርም፥ ዐመፃን የሚናገር በፊቴ አይጸናም። 8 ዐመፃን የሚያደርጉትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ከተማ አጠፋቸው ዘንድ፥ የምድርን ኀጢአተኞች ሁሉ በማለዳ እገድላቸዋለሁ። |